ተኽለ ተስፋዝጊ

0
1567

ሐምሌ ወር ሲመጣ ይህ ሰው ትዝ ይለኛል። ሁሌም ዘፈኖቹን ስሰማ ልቤ የሆነ ሀዘን ይሸብረዋል። በህይወት በነበረበት ወቅት የሰራቸው ስራዎች ከስሙ በላይ የገዘፉና በአብዛኛው ሰው ዘንድ የሚታወቁ ናቸው። ሰውየው በግሉ አልበም ባኖረውም በራሱ ስቱዲዮ ዉስጥ ቀድቶ ያስቀመጠው ዘፈኖቹ ብዙ ናቸው እንዲሁም ከትውልድ ቦታው አስመራ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ከሮሃ ባንድ ጋር በሰራቸው ስራዎች ይበልጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ይታወቃል፤ ተኽለ ተስፋዝጊ። አንዳንድ መዚቃውን የሚያዳምጡ ሰዎች ሲናገሩ ከሁለት እና ከሶስት በላይ አልበም መሆን የሚችሉ መዚቃዎች አሉት ይላሉ። ከ20 ዓመት በፊት እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ በተሰሙ መዚቃዎች በአልበም ደረጃ በህይወት እያለ ባያወጣም መዚቃዎቹ ተሰብስቦ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

ስለዚህ ሰው በመጀመሪያ ደረጃ የሰማሁት በሁለት ሺዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በሸገር ኤፍ ኤም ይተላለፍ በነበረው የዜማ ማህሌት ዝግጅት ወቅት ነበር። ከዛ በፊት ዘፈኖቹን በተለያየ መንገድ ሰምቼ የማውቅ ቢሆንም ሰውየው ማን ይሁን ምን ይሁን ብዙ አላውቅም ነበር። በኋላ በአንድ አጋጣሚ ዝግጅታቸው ላይ ማህተመ ሃይሌና ዳዊት ይፍሩ የተኽለ ተስፋዝጊ ስራዎች ዘክረው አለፉ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ነገሮች ማሰብ ጀመርኩ ስለ ተኽለ ሙዚቃዎቹንም መሰብሰብ ጀመርኩ፤ ስለእርሱ ማን ምን አለ አልኩ፤ በቃ ብዙ ነገር …።

በዝግጅቱ ላይ ስለ ስራውና ከሮሃ ባንድ ጋር ስለ ሰራቸው ድንቅ ዘመን አይሽሬ ስራዎች እንዲሁም ትንግርትና አሳዛኝ ስለሆነው አሟሟቱ በዳዊት ይፍሩ አንደበት ብዙ ተባለ …ተክሌ የራሱ በካሴት ሙዚቃዎች ባይኖሩትም በትግርኛ ሙዚቃ አፍ የሚያስከፍተን ኪሮስ አለማየሁ እንቁላል ፋብሪካ በሚገኘው ስቱድዮ አስቀርፆ አቀናብሮለት ለህዝብ አድርሶ ነበር። የተክሌ አብዛኛው ሙዚቃዎች ከራሱ ህይወት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው ይታወቅበታል ።እና ይህ ብርቱ ሰው ብዙ መስራት በሚችልበት ወቅት በአስደንጋጭና በአሳዛኝ መልኩ ህይወቱ አልፏል በዘመነ ደርግ። ወቅቱን የሚያስታውሰው ዳዊት ይፍሩ … በጊዜው ብዙ መዝናኛ ቦታና የሙዚቃ ስፋራ ወደ ነበረው ንፋስ ስልክ ዝግጅታቸው ሊያቀርቡ ይሄዳሉ፤ ከዛ ዝግጅታቸውን አቅርበው እንደ ጨረሱ እነ ዳዊት በሌላ መኪና ሳያመሹ ከአንድ የቡድን አባል ጋር በመሆን ወደ ቤት ይሄዳሉ። ተኽለ ተስፋዝጊ ከወዳጆቼ ጋር አመሻለው በማለቱ እዛ ይቀራል። እነ ዳዊትም በመንገዳቸው ላይ የቆመ ከባድ መኪና ሊገጩ ሲል ዳዊት ለሹፌሩ መኪና መኖሩን ነግሮት ይተርፋሉ ። ከእነርሱ በኋላ እየነዳ የመጣው ተኽለ ግን እነ ዳዊት ያለፍትን የቆመ ከባድ መኪና ጋር ተጋጭቶ በአሳዛኝ መልኩ ህይወቱን ያጣል ።

እርሱን በህይወት ብናጣውም ቋንቋ ባይገባንም ዘፈኖቹን ዛሬ ድረስ እንወደዋለን። በጥቂቱ ዘፈኖቹን ለመጠቆም ያክል …
ሳባ ሳቢና 
ሚስጥራዊ ደብዳቤ 
ፍቅረይ ተለመኒ
ከም ድላየይ 
ንብዓት ተመግበይ 
ምልክቲ ጓል ሄዋን … ይጠቀሳሉ

በተለያየ ወቅት የተኽለ ስራዎች በተለያዩ ድምፃዊያን ወደ አማርኛ ግጥም ተቀይረው ለህዝቡ ቀርበዋል ። በመጨረሻም ዛሬ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሰላም ድርድር ከኤርትራ ጋር እየተደረገ ባለበት ወቅት ከአስመራ የበቀለውን ተኽለ ተስፋዝጊን አስታወስኩት።

በዳግም ታምሩ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.