ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ ነጥሎ ማየት ለምን አስፈለገ?

2
540

በፈቃዱ ዓለሙ

የትግራይ ህዝብ ከቋንቋ በስተቀር ከአማራው ህዝብ ጋር በሥነ ልቡና፣ በባህል፣ በአመጋገብ፣ በአኗኗር፣ እና በመሳሰሉት የተሣሠረ ህዝብ ነው፡፡ አኔ ይህን የምለው በጥቂቱም ቢሆን ከገጠር እስከ ከተማ በሥራ አጋጣሚ ስለማውቀው ነው፡፡ በተለይ ወደ ገጠሩ አካባቢ ጎራ የማለት እድል ለገጠመው ሰው እንግዳ መሆኑን ሲረዱ ስስት የማያውቅ ፊታቸውን ፈገግ አድርገው ወደ ቤት ካልገባህ ብለው እንደ ዘመድ የሚንሰፈሰፉ ንጹህ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ወደ ቤት አልገባም ብትል እንኳን ጓዳውን ባታይም እቤት ውስጥ ያለውን ሁሉ ካልቀመስክ ብለው በኢትዮጵያዊ ለዛና ጨዋታ ያስተናግዱሃል፡፡ መቼም የማልረሳው አጋጣሚ ቢኖር አንድ ዶክመንተሪ ፊልም ለመሥራት ወደ ምሥራቁ የትግራይ አካባቢ ዘልቄ ነበር፡፡ ሰዓቱ የምሳ ሰዓት ስለነበር ቤተሰቡ በሙሉ ገበታውን ከቦ ሊበላ ሲል ደረስን፡፡ ታዲያ እኛ እንደረስን ሁሉም ቤተሰብ ተነሥቶ ያን ገበታ ለእኛ ለቆ እኛን ማስተናገድ ሽር ጉድ እያሉ እነዛ ትግራዋይ እንዴት ከልቤ ይጠፋሉ፡፡ አክሱም ጽዮን ላይ በየወሩ ለተከታታይ ሰባት ቀን ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ከተማዋን ዞረው የሚጸልዩት ዋጋ እንዴት ከአእምሮዬ ይጠፋል፡፡

በተለይ ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ካልሆንክ በቃ አንተ ንጉሥ ነህ፡፡ በትግራይ ክልል እንግዳ የፈጣሪ ያህል ይከበራል፡፡ በስሜ የተቀበለ ሁሉ በሰማይ ያለው አባቴ እንዲሁ ይቀበለዋል እንዲል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ ህዝቡ በአጠቃላይ ቸርና ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ ነው፡፡ እነ እንትና ህወሃት እና አንዳንድ የህወሃት ደጋፊዎች ግን ከዛ ህዝብ አብራክ የወጡ አይመስለኝም፡፡ ባለፈው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስለትግራይ ህዝብ ቸርነትና ሩህሩህነት እያለቀሰ ሲናገር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰማው ይመስለኛል፡፡  ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ለይቶ ማየት እንደሚገባ የተናገሩት፡፡

የሆነ ሆኖ በስሙ የተነገደበት እንጅ ዛሬም ድረስ ወደ አንዳንድ የትግራይ አካባቢ ብትሄዱ ከመንገድና ከመብራት ውጭ ሌላ ምንም ያገኘው ጥቅም የለም፡፡ ህዝቡ አሁንም በችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለብዙ ወንድሞች መናገር የምፈልገው የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ነጥሎ ለማየት የሚፈልግ ሰው ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ ትግራይ አካባቢ ሄዶ መመልከት አለበት ባይ ነኝ፡፡ ብዙዎቸ መቀሌ ደርሰው ስለመጡ የትግራይን ኹኔታ በመቀሌ ዓይን እየተመለከቱ ችግር ውስጥ ሲገቡ አያለሁ፡፡ መቀሌም ብትሆን ከመቀሌ ያለፈ ትሩፋት ለሌሎች አካባቢዎች የሚተርፍ ነገር የላትም፡፡

 

 

ታዲያ አውነታው ይሄ ከሆነ ከወደ ህወሓት በኩል እስካሁን በትላንትናው የፓርላማ ውሎ ምንም የተባለ የለም፡፡ ምክንያቱም በፓርላማ አባላት ሲጠየቁ የነበሩ ጉዳዮች በሙሉ ህወሓት ኢህአዴግን ስለሚመለከቱ ነው፡፡ ትግራይ ኦን ላይን፣ አቶ ዳንኤል ብርሃነ፣ አቶ አብርሃ ደስታ እና የመሳሰሉ ህወሓት ወለድ አቀንቃኞች በትላንትናው የፓርላማ ውሎ ትንፍሽ አላሉም፡፡ ምን አልባት ጊዜ ወስዶ ማየትን መርጠው ይሆናል፡፡

አቶ አብርሃ ደስታ

እኒህ የአረና ሊቀ መንበር የኢህዴግ ሥራ አስፈጻሚ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ጉዳይ ላይ (ቀደም ሲል በአቶ መለስ ዜናዊ አማካኝት በፓርላማ ፊት ከህዝብ ተደብቆ የተላለፈውን) ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ መነሣቱ ወቅታዊና እንደ ኢሮብ ዓይነት ብሄርን ከሁለት የሚከፍል ጉዳይ ነው እያሉ ሲከራከሩ ሰንብተዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአብርሃ ደስታን መከራከሪያ ሃሳብ አፈር አልብሰውታል፡፡ እንዲህም አሉ… “በአፍሪቃ ውስጥ በቅኝ ገዥዎች አርቲፊሻል የድንበር ክለላ ወይም እነሱ አስምረው በሰጡን ካርታ ብዙ የአፍሪቃ ወንድሞቻችንን ተከፋፍለው እስከአሁን የድንበር ችግሩ ከፍተኛ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኤርትራ ውስጥ ስንት እና ስንት ወገኖች በህወሃትና በሻብእያ ምክንያት ከዘመዶቻቸው ጋር ተቆራርጠው እንደቀሩ አቶ አብርሃ ድስታ የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ይሄ የፈረደበት ኅዳር 29 ሲመጣ ካልሆነ በቀር የት እንዳሉ እንኳን ስማቸውን ጠርተው የማያውቁትን የኢሮብ ብሄር እንደ ሽፋን ሲጠቀም አላፈረም፡፡ ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም አብርሃ ደስታና ህወሃት የተባብሩ እስኪመስል ድረስ በባድመ የሚኖሩ ዜጎችን ሰላማዊ ሰልፍ እሰከማስወጣት ደርሰዋል፡፡ እዚች ላይ  “ሌቦቹ መዝረፋቸው ሳያንስ ልክ እንዳልተነቃባቸው ሁሉ ሲዶልቱ መዋላቸው ያሳምማል” ይሉሃል ይሄ ነው፡፡

በኬኒያ ውስጥ ያሉ የገዳ ሥርዓት አራማጆች ከኦሮሚያ ጋር ያላቸው የቋንቋ፣ የባህል ዘይቤ ተመሳስሎት ለአብርሃ ደስታ አልታየውም፡፡ እንዲሁም በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያ፣ በሱዳን እና በሩዋንዳ ውስጥ በልዩ ልዩ ቦታዎች በቋንቋ፣ በባህል እና በአመጋገብ የሚመሳሰሉ ህዝቦች በቅኝ ገዥዎች ተከፋፈለው መኖራቸው ምንም እንዳልጠቀማቸው አቶ አበርሃ ደስታ እና ህወሃት እያወቁ መዶለታው አላሳፈራቸውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አሉ የእኛ ዓላማ ይሄ ተለያይቶ መኖር ለማንም አልጠቀመም እና የሁለቱ ሀገር ወንድማማቾች መነጋገር፣ መጠያየቅ እና በሰላም መኖር መጀመር አለባቸው ነው ያሉት፡፡

 

ህወሃትና የማእከላዊ ኮሚቴው መግለጫ ሲታወስ

የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት በሀገራዊና በክልላዊ ጉዳዮች ላይ ባለ 9 ነጥብ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ውስጥ

“በኢትዮ-ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ጉዳይም ሆነ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያየዘ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ኢህአዴግ ምክር ቤት ሳይቀርቡ፣ አጋር ድርጅቶች ሳይሳተፉበት እና የሚመልከታቸው አካላት በዝርዝር ሳይወያይበት እንደመጨረሻ ውሳኔ ተወስዶ ለህዝብ ይፋ መደረጉ አንድ ጉድለት እንደሆነ ማእከላዊ ኮሚቴዉ ደምድሟል።”

እና

“የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከዳር እስከዳር በከፍተኛ ሃገር ፍቅር የተሳተፉበት እና መስዋእት የከፈሉበት ጉዳይ በዝርዝር ሳይወያዩበት እና በቂ መተማመን ሳይደረስበት በሚዲያ ይፋ መግለጫ መሰጠቱ ህዝባችን ላይ ቅሬታ፣ ቁጣና መደነጋገር የፈጠረ በመሆኑ አንድ ሌላ ጉድለት ነው።” የሚሉት በአንደም በሌላም በፓርላማ አባላት ተጠይቀው አጥጋሚ መልስ ተሰጦባቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሃትንና የትግራይን ህዝብ አንድ አድርጎ የማየት ችግር መስተካከል አለበት ያሉት ለዚህ ነው፡፡ ህወሃት ሁሌም ቢሆን ድብቅ ነው፡፡ የኢትዮ-ኤርትራን ጉዳይ ላለፉት 18 ዓመታት ደብቆ እዚህ አደረሰን፡፡ ቀጠለና ቀደም ሲል ህወሃት ራሱ ባሳለፈው አሳብ እንገዛለን ብሎ ከደመደመ በኋላ ለምን በሚዲያ ተገለጸብኝ ዓይነት ክስ ቢጤ መዶለት ጀመረ፡፡ ህወሃት ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮችን ለህዝብ ይፋ አያደርግም ነበር፡፡ ጥቂቶች አለ እንጅ ጠቅላይ ሚኒስተሩ በብዛት በህወሃት ውስጥ የተሰገሰጉ ባለሥልጣናትና ሌሎች በትግራይ ህዝብ የሚነግዱ ሰዎች ናቸው ያን ምስኪን ህዝብ የሚያስተቹት፡፡ መዶለቻ ቢያጡ በኢሮብ ብሄር መጡ፡፡ መዶለቻ ቢያጡ ለምን በሚዲያ ተነገረ አሉ፡፡ መዶለቻ ቢያጡ ለምን ሰዎች ተፈቱ፤ ለምን ሰዎች የሰላም አየር ተነፈሱ አሉ፡፡ መዶለቻ ቢያጡ ለምን አሸባሪዎች ተፈቱ አሉ፡፡ በየማረሚያ ቤቱ ያሉ ደብዳቢዎች፣ ጥርስ አውላቂዎች፣ እግር ቆራጮች፣ ብልት ቆራጮች፣ ገዳዮች እነሱ ናው፡፡ ይሄን ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው በይፋ ለህዝቡ ከአሁን በኋላ በድብቅ የሚሠራ ሥራ የለም ያሉት፡፡ አሸባሪዎች እኛ ነበርን፣ ህግ ያላከበርነው እኛ ነን፣ ፍትሃዊ ያልነበርነው እኛ ነን….በእነዚህ ደግሞ ድርጅቱ ራሱ ንስሀ የገባባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡

ህወሃት ለብሄረሰቦች ነው የቆምኩት ይበል እንጅ ህዝቦችን በጎጥና በቋንቋ እያነታረከ በብዙ አካባቢዎች አንዱ አንዱን የጎሪጥ እንዲያይ ትልቁን ድርሻ የተወጣ ኢ-ዲሚክራሲያዊ ግንባር ነው፡፡ “ሰውን እየጠሉ፤ ሌላውን እርስ በእርስ እያጣሉ ልጅ መውለዳቸው ደግሞ ይገርማል” አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤተ መንግሥቱ ጉዳይ ዛሬም በዚህ ሴራው እንዳልቆጠበ ቢገባቸው፡፡

2 COMMENTS


 1. Notice: get_user_by_email is deprecated since version 3.3.0! Use get_user_by('email') instead. in /home/addisinsight/public_html/wp-includes/functions.php on line 3853
  Mehret

  Thats not how I understood the statement from TPLF. It says it should have been discussed by all parties before it was declared as an official position. That means giving space for debate and saying the PM adequetly responded to the question of Badem is like saying Meles properly addressed the Asseb situation. 🙂


 2. Notice: get_user_by_email is deprecated since version 3.3.0! Use get_user_by('email') instead. in /home/addisinsight/public_html/wp-includes/functions.php on line 3853
  ጉልላት21

  yea, it seems but the reality
  is as the PM said it in the Parliament the day before yesterday.

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.