ህዝብና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን ያመላከተው የህወሃት/ኢህአዴግ ድርጅታዊ ውሳኔዎች

0
283

በፍቃዱ አለሙ

በኢህአዴግ ቤት አሁንም በተስፋ ውስጥ ብዠታው ቀጥሏል፡፡ የትኛውን አንሥትን የትኛውን እንደምናወራ ግራ ያጋባል፡፡ በአንድ ምሽት ብዙ ያልተጠበቁ ለውጦች እየተከናወኑ ነው፡፡ እኛ ሀገር ዜናና ወቅታዊ መረጃ አቀባይና ተንታኝ መገናኛ ብዙኀን ቢኖሩን ኖሮ ትላንት ምሽት የተላለፉት ውሳኔዎች ብቻ ጉዳዮችን በባለሞያ እያስተቹ ለመተንተን 24 ሰዓት አይደለም አንድ ሳምንት እንኳ አይበቃቸውም፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው ዛሬም በየሚዲያው የሚሰማው ከእለት ዜና ውጭ ጉዳዮችን በደንብ በጥልቀት የሚያወያይ በተለይ ከህዝብ አንተጻር ማለቴ የለም፡፡ ይሄኔ ኹነቱ በአፍሪካ ወይም በምእራባውያን ተከናውኖ ቢሆን የመንግሥት አፈ ቀላጤው ሬዲዮ ፋና ሳይቀር ለውጭ ትንታኔ ይመርጠው ነበር፡፡  በዚህ ረገድ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በጣም ተሽለው ተገኝተዋል፡፡ የአንድ “ባድመ” ድንበር ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ እንዳልሆነ ቢያንስ ተራው ዜጋ በሰፊው ከተለያዩ እሳቤዎች አንጻር እየተወያየበት ነው፡፡በዘህ አጋጣሚ እንዲህ ዐይነት አተያዮች የማይጥማቸው ሰዎች እንዳሉ እየሳሰብኩ የግል ምልከታየን ግን እቀጥላለሁ፡፡

ኢህአዴግ አሁንም የህዝብን ሳይሆን የፓርቲ ውሳኔውን ቀጥሏል፡፡ ህዝብ እንዲናገር፤ በአገር ጉዳይ ላይ ድምፅ እንዲሰጥ ፡ ወደ ሊበራል ለሚደረገው ጉዞ የተወሰነው የእነ አየር መንገድ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ እና ሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች ሽያጭ እንዲሁም ባድመ ለኤርትራ ትገባለች የሚሉት ከውሳኔዎቹ መካከል ናቸው፡፡ ኢህአዴግና ዶክተር ዐቢይ በቀጣይ የነሐሴ ድርጅታዊ ስብሰባ የሚታዩ ቢሆንም ግን አንዳንድ ውሳኔዎች ከአሁኑ የሀገራችን ማኅበረ-ፖለቲካ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

የባድመ ጉዳይ ከዛሬ ስንት እና ስንት ዓመት በፊት ነበር የተወሰነው፡፡ ግን ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ዛሬ ገና ተቀብላ ለመተግበር እንደወሰነች ተደርጎ ተነገረ፡፡ በዚህ ሳያበቃ የኢትዮጵየ ህዝብ በድንበር ጉዳይ እንደማያገበው ኢህአዴግ በግልጽ አቋሙን አሳይቷል፡፡ የድንበሩ ጉዳይ  በህዝብ በእንደራሴዎች በኩልም ይሁን በሀገር ደረጃ ምንም ድምፅ ሳያሰሙ ውሳኔው ተላልፏል፡፡ እንዴትስ ትላንት ደርሶ አጀንዳ ሆኖ ወዲያው ተወሰነ ብሎ ለሚጠይቅ ጋዜጠኞ ወይም ፖለቲከኛ መልሱ ዥዋዥዌ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የባድመ ጉዳይ የሁለቱ ሀገሮች ወንድማማቾች ሞት ብቻ መስሎ ይታያቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ባድመ ለኤርትራ ተላልፎ መሰጠቱ ብቻ ይታያቸዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ከዚህ የድንበር ውሳኔ ጋር ተያዘ የሚመጣው ጉዳይ ወሳኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ስትቀበል እንደ ወራሪ ትቆጠራለች ወይስ አትቆጠርም? ኤርትራስ ሌሎች ጥያቆዎችን ልታነሣ ትችላለች አትችልም?  እና መሰል አሳቦች ወደ ፊት ብዙ እንድንጠብቅ ያደርገናል፡፡

ስንቱ ደሀ በኢኮኖሚው የዋጋ ግሽበት ምክንያት የመግዛት አቅሙ እየተዳክመ ለውጥ በሚጠብቅበት ሰዓት የባድመ ጉዳይ ቀደመ…ስንት እና ስንት የተደራጀ ሌባ ባለበት ሀገር የሙሰኞች ጉዳይ አልቀደመም፡፡ ዲሞክራሲንና ነጻ ገቢያን የተደራጁ ሌቦች ወይም ሙሰኞች አደገኛ መሆናቸውን በመድረክ በመናገር ላይ ዛሬም ተነገረ፡፡ ትላንት እና ከትላንት ወዲያ ግን ሙሰኞች ግልጽ ባልሆነ በይቅርታ ስም ተፈተዋል፡፡ በኢኮኖሚው ላይ የተወሰደው ማሻሻያ አሁንም እነዛን የተደራጁ ሌቦች የሚጠቅም እንጅ አንዳች ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ባዶ ድካም ያደርገዋል፡፡ በ100 ብርና በ 500 ብር ካፒታል ተነሥቶ በአንድ ዓመት እና በሁለት ዓመት ውስጥ ቢሊዮነር በሚሆኑባት ሀገር፤ እነማን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በበላይነት እንደተቆጣጠሩት እየታወቀ “ቅድሚያ ለሀገር ውስጥ” በሚል ፈሊጥ ለእነማን ለመሸጥ እንደተዘጋጀ ይታወቃል፡፡

ትልቁ የአፍሪቃ ኩራት የሆነው አየር መንገዳችን መላው አፍረቃ ብሎም ዓለም እያደነቀው ያለ ተቋማችን ነው፡፡ ብዙ አፍሪካውያን በኢትዮጵያአየር መንገድ እንዴት ደስ እንደሚላቸው ለሚያውቅ ሰው ለመሸጥ አይዘጋጅም፡፡  አየር መንገዱ በኢትዮጵያውያን  መተዳደሩ ብዙዎቹ ያስደንቀቸዋል፡፡ ለውጡም እንዲሁ፡፡ ይሄ ጉዳይ ወይ የእኛ ሀገር ባለሀብት ሌቦች ይገዙታል ወይም ደግሞ ባርነት ይጠብቀዋል፡፡

የዐዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዞ አንድም ኢህአዴግን ከገባበት ዝቅጠት ለማዳን ሁለትም የህዝቡን ችግሮች በአዲስ አሠራር አስተካክላለሁ የሚሉት ጉዞዎች ሄደው ሄደው የዐቢይን ልፋት መና እንዳያደርጓቸው እሰጋለሁ፡፡ ይሄ ምቀኝነት ሳይሆን የፖለቲካው አሰላለፍና እንዲህ ደርሰው የህዝብን ድምፅ ያላካተቱ ውሳኔዎች ቀላል እንደልሆኑ ለማመላከት ነው፡፡  ምን አልባት ከባድመ  ውሳኔ ጀርባ ያለው ጉዳይ በጥልቀት ከታየ፤ ግዙፎቹ የመንግሥት ተቋማት ወደ ፊት እነማን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንደ ሚገዟቸው ከታየና የህዝብ ጥያቄዎች ተደማጭነት  ካገኙ እና መስተካከል ከቻሉ እሰየው፡፡ ነገር ግን ይሄ ሁሉ ቂልነት እንደሆነ አምናለሁ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን የማየትና የመቃኘት ልምድ ቢኖረው  አሁን እየተዘጋጀበት ባለው መግለጫ ውስጥ ቢያንስ አንዳንድ ማብራሪያዎቸን ለማካተት እድል ይኖረዋል፡፡

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.