የመዲናዋ መስፋፋት ጥያቄ

0
862

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የዓለም ኤንባሲዎች ከተማ፣ የብዙ ዲፕሎማት መኖርያ፣ የኢትዮጵያ አንድነት እና የብሄር ብሄረሰቦች ጥምረት ተምሳሌት. . .ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል ለአዲስ አበባ ከተማ ወይም ለአፍሪካ መዲና። የአፍሪካ መዲና የሚለው ስም እርግጥ ደስ ይላል። ብቻ መዲናችን ባሁን ወቅት ከዓለም ትላልቅ ከተሞች ተርታ ትሰለፋለች አንዲሁም የከተማዋ በተራሮች መከበብ እና በተንጣለለ ሜዳ ላይ መቀመጥዋ በተለይ በዓለም ከሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ተወዳጅና ተመራጭ የሚያደርጋት በምቹ የአየር ሁኔታዋ ምክኒያት ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎች ቆይታቸው አንዲሁም ኑሯችው በአዲስ አበባ ከትሟል፤ የኢትዮጵያ ተወላጆችም ከአራቱም አቅጣጫ ወደ መዲናዋ በመምጣት እየከተሙ ናችው። ወደ ዋናው ሃሳቤ ከመግባቴ በፈት የአዲስ አበባ ከተማ ታሪክን እስኪ እንቃኝ።
የተለያዮ መዛግብት እና መርጃዎች አንደሚያመላክቱን አፄ ምኒልክ የሸዋ ንጉስ ሆነው ሲነግሱ መቀመጫቸው እንጦጦ ላይ ነበር። ነገር ግን ማገዶም ሆነ ውሃ በማጣት አካባቢው መንደር ለመመስረት አይመችም ነበር፤ ስለዚህ መስፈሪያው በውኑ የጀመረበት ከተራራው ትንሽ ወደ ደቡብ በሚገኘው ሸለቆ ውስጥ በ1878 ዓ.ም ነበረ። በመጀመሪያ እቴጌ ጣይቱ ፍልውሃ ምንጭ አጠገብ ለራሳቸው ቤት ሰሩ። ይህ ምንጭ ለኦሮሞ ህዝብ ፊንፊኔ ተብሎ ይጠራ ነበር። እዚህም እርሳቸውና የሸዋ ቤተመንግስት ወገን መታጠብ ይወዱ ነበር። ከዚያ በኋላ ሌሎች መኳንንቶች ከነቤተሰቦቻቸው በአቅራቢያው ሰፈሩ፤ አፄ ምኒልክም የሚስታቸውን ቤት ቤተመንግስት እንዲሆን አስፋፉትና እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ መንግስት ሆኖ ቆይቷል። አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት በሆኑበት ወቅት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆነች። ከዚያ ጀምሮ ከተማዋ ቀስ በቀስ ማደግ ጀመረች።

በ1928 ዓ.ም የጣሊያን ፋሺስቶች ከተማዋን ወረው ዋና ከተማቸው አደረጉዋት፤ እስከ 1931 ዓ.ም ድረስ የኢጣልያ ምስራቅ አፍሪካ ገዥ መቀመጫ ነበረች። የኢጣልያ ሰራዊት በኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎና በእንግሊዝ ዕርዳታ ከተሸነፈ በኋላ፤ አፄ ሃ/ስላሴ ከ5
ዓመት ስደት በኋላ በ1933 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። ወዲያው ከተማይቱ እንደገና ዋና ከተማቸው እንድትሆንም መሰረታዊ ስራዎችን መስራት ጀመሩ። በ1955 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (OAU) እንዲመሰረት የበኩላችው ትልቁን ድርሻ ሰላበረከቱ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ሆነ። ይህ ድርጅት በ1994 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት (AU) ተተካ፤ ዋና መስሪያ ቤቱም እዚሁ አዲስ አበባ ላይ እንዲቀጥል ተደርጓል። እንደዚሁም በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘውም አዲስ አበባ ውስጥ ነው። በዚህም ምክኒያት የአፍሪካ ዲፕሎማት ኑራቸው እና ስራችው በመዲናዋ እንዲሆን ተገደዋል።

አዲስ አበባ ከተማ ባሁን ወቅት ወደ 6.6 ሚልዮን የሚጠጋ ህዝብ ብዛት አላት። የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ወደ 107 ሚልዮን ገደማ ነው። ይህ ማለት ከኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 6.6 በመቶ አካባቢ የሚሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በመዲናዋ ይኖራሉ። የመዲናዋ ቆዳ ሰፋት ግን 527 ኪ.ሜ2 ነው። የኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት ደግሞ 1.104 ሚልዮን ኪ.ሜ2 ነው። ይህ ማለት ከኢትዮጵያ ቆዳ ሰፋት 0.05 በመቶ የሚያክል ቦታ ነው የአዲስ አበባ ከተማ ሰፋት። ኦሮምያ ክልል ከሀገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 33.05 በመቶ የህዝቡ ብዛት 36.7 በመቶ፣ ሶማሌ ክልል በቆዳ ስፋት 19.82 በመቶ የህዝቡ ብዛት 6.0 በመቶ፣ አማራ ክልል በቆዳ ስፋት 17.34 በመቶ የህዝቡ ብዛት 23.3 በመቶ፣ ደቡብ ክልል በቆዳ ስፋት 10.28 በመቶ የህዝቡ ብዛት 20.4 በመቶ፣ ትግራይ ክልል በቆዳ ስፋት 5.53 በመቶ የህዝቡ ብዛት 5.8 በመቶ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቆዳ ስፋት 4.3 በመቶ የህዝቡ ብዛት 0.9 በመቶ፣ ጋምቤላ ክልል በቆዳ ስፋት 2.4 በመቶ የህዝቡ ብዛት 0.4 በመቶ፣ አፋር ክልል በቆዳ ስፋት 2.03 በመቶ የህዝቡ ብዛት 1.9 በመቶ፣ ድሬዳዋ ክልል በቆዳ ስፋት 0.15 በመቶ የህዝቡ ብዛት 0.5 በመቶ፣ ሐረር ክልል በቆዳ ስፋት 0.03 በመቶ የህዝቡ ብዛት 0.2 በመቶ የሀገሪቱ ድርሻ ይሸፍናሉ። አዲስ አበባ ክልልና የሀገሪቱ ዋና ከተማ ከመሆን አልፋ የአፍሪካ መዲናም ሆናለች። ግን የመዲናዋ ስፋት ካላት ህዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ ሰፊ በመሆኑ በመዲናዋ የሚኖሩ በርካታ ህዝቦች በሌሎች ከተሞች ያልተለመደው ዓይነት አኗኗር ዘዴ ተያይዘውታል። በደርግ ጊዜ እና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ግዜ የግለስቦች የነበሩ ቤቶች ወደ መንግስት እጅ ገብተው እድሜ ለቀበሌ ክራይ ቤቶች ምስጋና ይድረሰውና የቤት ደባል ወይም ለአንድ ቤተስብ የሚሆን ቤት ለተለያዩ ቤተሰቦች ቤቱን ተከፋፍሎ መኖር በከተማዋ ባህል እየሆነ መጥቷል። የቤት ደባል ዓይነት አኗኗር ብዙዎቹ ተቀብለዉት እየነሩም ነው። ነገሩ ሌላ ምርጫ ስለሌላችው የቤት ደባል ከመሆናችው አይቀሩም። ምክኒያቱም በመዲናዋ ህዝብ ብዛት ስለጨመረና በከተማዋ የሚገኙ ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ ሰላልተቻለ ነው። ግን እንዴት አዲስ አበባ ከተማ ከተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ታወደድራለክ ትሉ ይሆናል። እያወዳደርኩኝ ሳይሆን አዲስ አበባ አንደክልልና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በመሆንዋ እንዲሁም የአፍሪካ መዲና ስለሆነችም የግድ መስፋፋት አለባት። ምክኒያቱም በከተማዋ የህዝብ ብዛት በየዓመቱ 3.8 በመቶ ጭማሪ ያሳያል። ስናሰላው በ2022 ዓ.ም ማለትም ከ12 ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ወደ 139 ሚልዮን ገደማ ይሆናል። የአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ የህዝብ ቁጥር ጭማሪ ሲሰላ በየዓመቱ 251 ሺ ተጨማሪ ህዝብ ታስተናግዳለች፣ ከ12 ዓመት በኋላም አሁን ካላት ህዝብ ሲደመር ወደ 9.9 ሚልዮን ህዝብ በመዲናዋ ኗሪ ይሆናሉ። ግን የከተማዋ ስፋት ከ527 ኪ.ሜ2 ሳይጨምር ባለበት ይቀጥላል።
እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜጎች በተለያዮ የኢትዮጵያ ግዛቶች ላይ መዋዕለንዋይ(investment) እያስፋፉ በመሆናቸው ዋና መስራያ ቤትና መቀመጫቸው በአዲስ አበባ ከተማ ነው የሚያደርጉት፤ የከተማዋ ስፋት ስላነሰ በመዲናዋ የሚኖሩ ህዝቦች የኑሮ ደረጃ ሰፊ ልዩነትም እያመጣ በመሆኑ ገቢያቸው ከፍተኛ የሆኑት ኑራቸው በመጠኑ የተሻለ እየሆነ መጥቷል። በተቃራኒ ደግሞ የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑት ማህበረሰቦች ኑራቸው በጣም እያሽቆለቆለ መሆኑን ሁላችንም የምናውቀው ነው። ለዚህ ክስተት ድግሞ የመዲናዋን ቆዳ ስፋት መጨመር ሰላልተቻለ ነው። በእርግጥ በክፍለ ከተማ ቀበሌዎች ስር ያሉት ቤቶች ክራይ ዋጋ ዝቅተኛ ናቸው። ነገር ግን ከ15 እና 20 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ከተማ የከተሙ ማህበረሰቦች የቀበሌ ክራይ ቤቶችን ተከፋፈለው እየኖሩበት ነው። ከ15 ዓመታት በፊት ወደ መዲናዋ የሰፈሩት ደግሞ እድለኞቹ የኮንደምንየም ቤት ባለቤት ሆነዋል፤ የተቀሩት ደግሞ እጅግ በጣም ውድና ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ቤት ተከራይተው ከኑሮ ጋር ትግል ተያይዘውታል። የአዲስ አበባን እድገትና መስፋፋት ማቋረጥ አይቻልም። አንድን የዛፍ ችግኝ እድገቷን ማዘግየትም ሆነ ማስቆም አይቻልም። ልክ እንደ ተክሎች እድገት የከተሞችም እድገት ተፈጥሯዊ ባህሪ አለው። የአዲስ አበባን እድገትና መስፋፋት መግታት አይቻልም። አዲስ አበባ የኢትዮጲያ ማዕከል ሆና መቀጠልዋ አይቀርም። በኦሮምያ ክልል እምብርት ላይ የተወለደች ከተማ መሆኗን መቀየርም አይቻልም። አዲስ አበባ ከተማ ወደ ጎን እንዳትስፋፋ እንቅፋት ከሆነባት መካከል በዙርያዋ የተከበበችው በኦሮምያ ክልል ከተሞች ስለሆነ ለማስፋፋት አዳጋች ይሆንባታል። ምክኒያቱም አዲስ አበባ የምትጠይቀው ቦታ የገበሬዎች እርሻ ቦታ ሳይሆን የኦሮምያ ክልል ከተሞች ናቸው። በደቡብ ሱሉልታ፣ በሰሜን ዱከም፣ ቢሸፍቱ እና ሰንባታ፣ በምዕራብ አዲስ አለም፣ በምስራቅ ሰንዳፋ ከተሞች አዲስ አበባን ከበዋት ይገኛሉ።

አዲስ አበባን ለማስፋፋት ማስተር ፕላን በወጣበት ጊዜ የነበረው ቀውስ ለሀገራችን ሌላ ጥቁር ጠባሳ ጥሎብን አልፏል። በሕገ መንግስት አንቀፅ 48 “የክልሎች ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንዲሆን ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር
ቤት የህዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወሰናል።” ይላል በሕገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረትም ሁለቱም ክልሎች ባለመስማማታቸው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ወደ ጎን መስፋፋቱን አቁሞ ወደ ላይ ሁኗል። በዚህ መሰረት መዲናዋ ላይ የምናያቸው ለውጦችም አሉ። ለምሳሌ በከተማዋ ያሉት የሪልስቴትና የቤት ግንባታ የገቢ ምንጫቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ ደረጀቶች የተናጠል ቤት(ቬላ ቤት) ማቅረብ ትተው የጋራ ቤቶች(ኮንድምንዬም ወይም አፓርታማ ቤቶች) መገንባት ሆኗል ስራቸው። ምክኒያቱም ከሚሰጣቸው የቦታ ውስንነት አንፃር ቤት ወደ ጎን መስራት ትተው ወደ ላይ ቤቶችን ደራርበው ከ10 ፎቅ በላይ በመስራት ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እየሆኑ ነው። አስቡት መኖርያ ቤት ተብሎ ግን በ10 እና ከዛ በላይ ፎቅ ላይ መኖርያ ቤቶች ተብለው ለህዝብ ሲቀርቡ፣ መዲናዋ አደጋ ወስጥ መሆንዋን ያመላክተናል። አንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለረዥም ጊዜ በቆርቆሮ ታጥረው የቆዩት ቦታዎች አሁን ግንባታ ተጀምሮባቸዋል። ነገር ግን እነዚህ በቅርቡ የተጀመሩት የቤቶች ግንባታ ቢጠናቀቁ ባሁን ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ ለሚኖሩ ህዝቦች ተደራሽ ይሆናልን? 12 ዓመት ሩቅ አይደለም በጣም ቀርብ ነው። ከ12 ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 139 ሚልዮን ሲጠጋ የአዲስ አበባ ድግሞ 9.9 ሚልዮን ህዝብ መኖርያ ትሆናለች ግን የመዲናዋ ሰፋት 527 ኪ.ሜ2 በላይ መስፋት የምትችል አትሆንም። እኔ በበኩሌ የአፍሪካ መዲና መስፋፋት አለባት እላለሁኝ ግን እንዴት በኦሮምያ ክልል ከተሞች ተከባለች እንዲሁም ሕገ መንግስትም በ አንቀፅ 48 መሰረት ሁለቱም ክልሎች ባልመስማማታቸው መዲናዋ መስፋፋት አልቻለችም። የመዲናዋ መስፋፋት ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል ግን እስከ ምቼ?

በናስር አብዱራሂም

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.