ከመጻሕፍት ገበታ

0
338

በኢትዮጵያ፡ ሊወሱ፡ የሚገባቸው፡ ነገር፡ ግን፡ የተረሱ፡ በግእዝም፡ ሆነ፡ በአማርኛ፡ የተጻፉ፡ በርካታ፡ መጻሕፍት፡ አሉ፡፡ ከእነዚህም፡ መካከል፡ በአፄ ተዌድሮስ ዘመን በ1857፡ በአለቃ፡ ዘነብ፡ የተጻፈው፡ መጽሐፈ፡ ጨዋታ፡ ሥጋዊ፡ ወመንፈሳዊ፡ ነው፡፡ ይህ፡ መጽሐፍ፡ በጨዋታ፡ እያዋዛ፡ የሚመክር ወግ ነው፡፡ተዝናኑበት፡፡

መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ

እግዚአብሔር፡ እስቲሻር፡ ሚካኤል፡ እስቲሞት፡ ምነው፡ በኖርሁኝ፡፡ ገብርኤል፡ ሲያንቀላፋ፡ ሩፋኤል፡ ሲደክም ፡ሐሰተኛው፡ ዲያብሎስ፡ ንስሐ፡ ይገባል፡፡

ክረምት፡ ሲመጣ፡ ሰማይ፡ እንዲከብድ፡ የጠሉትም፡ ሰው፡ ሲመጣ፡ እንደዚያ፡ ይከብዳል፡፡ ዘወትር፡ ከሚያጋድል፡ አህያ፡ ተሸክሞ፡ መሄድ፡ ይሻላል፡፡ ከማያስተካክል፡ መላክተኛ፡ የማለዳ፡ ወፍ፡ ትሻላለች፡ ምነው፡ ቢሉ፡ ንጋቱን፡ ትነግራለችና፡፡

ድንጋይና፡ ጭቃ፡ ቢቀጣጠሉ፡ ታላቅ፡ ቤት፡ ረጅም፡ ቅጥር፡ ይሆናሉ፡ እናንተም፡ መሬታውያን፡ ሰዎች፡ እንደዚህ፡ ብትረዳዱ፡ ጥበባችሁና፡ ኃይላችሁ፡ ከሰማይ፡ በደረሰ፡፡

ኮሶና፡ ክረምት፡ ፊት፡ ያመራል፡ ኋላ፡ ግን፡ ደስ፡ ያሰኛል፡፡ ድሪ፡ ምንድር፡ ነው፡ ገንዘብን፡ ለመቆራኘት፡ የተሠራ፡ ሰንሰለት፡ ነው፡፡ እሬት፡ መብላት፡ ቢለመድ፡ ባልተለቀቀም፡ ነበር፡ ዝሙትም፡ ላለመደው፡ ሰው፡ እንደዚህ፡ ነው፡፡

ጣዝማ፡ እጅግ፡ ብልህ፡ ናት፡ መሬት፡ ቀዳ፡ ገብታ፡ እንደዚያ፡ ያለ፡ መድኃኒት፡ የሚሆን፡ ማር፡ ትሠራለች፡፡ ምነው፡ እናንተ፡ ሰዎች፡ ወይ፡ ከፈጣሪ፡ ወይም፡ ከሰው፡ ብልሀትን፡ አትፈልጉምን፡፡

የምሥራች፡ ከሩቅ፡ አገር፡ በመጣ፡ ጊዜ፡ የሰው፡ ልብ፡ በደስታ፡ ባሕር፡ ይሰጥማል፡፡ እርጎን፡ ከፍቶ፡ ቢተውት፡ ዝንብና፡ ድመት፡ ይጫወትበታል፡ አገርንም፡ አቅንቶ፡ ሰው፡ ካላስቀመጡበት፡ ተመልሶ፡ ዱር፡ ይሆናል፡፡

ባባቱ የሚኮራ ሰው ጅል ነው የሰው አባቱ አንድ አዳም አይደለምን፡፡ ሴትን ወንድ አንድ ጊዜ ይደርስባታል መንታ ትወልዳለች እህልም አንዲት ፍሬ ተዘርታ ብዙ ታፈራለች ይህ ነገር ከቶ እንዴት ነው እንጃ ማን ያውቀዋል ያ የጠቢቦች ጠቢብ ያውቀው እንደሆነ ነው እንጂ፡፡ ፈረስ፡ በብረት፡ ልጓም፡ ይገታል፡ የሕዝብም፡ ልጓሙ፡ ንጉሥ፡ ነው፡ መቃብር፡ መልካም፡ ጐታ፡ ነው፡ ብስሉንና፡ ጥሬውን፡ ይከታልና፡፡ ወዳጅ፡ ቢወዱት፡ ይወዳል፡ መሬትም፡ ቢበሉት፡ ይበላል፡፡

በርበሬ፡ ላይን፡ ቀይ፡ ሆኖ፡ ይታያል፡ ምነው፡ ቢሉ፡ በብልሐት፡ ገብቶ፡ ሊለበልብ፡፡ ክፉ፡ ሰውም፡ ቀስ፡ ብሎ፡ ገብቶ፡ ኋላ፡ ነገሩን፡ ያመጣል፡፡

ቸር፡ ሰው፡ ለወዳጁ፡ ጠጅ፡ ነው፡ ፍቅሩ፡ ያሰክራልና፡፡ ዝናም፡ ከዘነመ፡ በኋላ፡ ቡቃያ፡ ያበቅላል፡ ንጉሥም፡ ከወደደ፡ በኋላ፡ ይሾማል፡፡

ሸክላ፡ እጅግ፡ ክፉ፡ ነው፡ ወሀ፡ አርሶ፡ አሠርቶት፡ መከታ፡ እየሆነ፡ እሳትን፡ ያስወጋዋል፡፡ ክፉም፡ ሰው፡ እንደዚያ፡ ነው፡፡ ወንፊት፡ ዱቄትን፡ እንዲነፋ፡ ዘርዛራም፡ ሸማ፡ ጠጅን፡ እንዲያወርድ፡ ባለቤቱም፡ ያልቻለውን፡ ምሥጢር፡ ሌላው፡ ሰው፡ አይችለውም፡፡

ቅቤ፡ ካይብና፡ ካጓት፡ እንዲለይ፡ በላይም፡ እንዲሆን፡ ጻድቅም፡ ሰው፡ እንደዚያ፡ ነው፡፡

በ ፀጋ ወ/ፃዲቅ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.