ወሳኙ ጉዳይ የዶክተር ዐቢይ የህዝብ ድጋፍ ምን ዐይነት ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል የሚለው ነው?

0
1108

በፈቃዱ ዓለሙ

ከመጋቢት 19፣ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ዶክተር ዐቢይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ምኒስትር ሆነው ከተመረጡበት ጊዜ አንሥቶ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝት  ልዩ ልዩ አሳቦች መንሸራሸራቸውን አላቆሙም፡፡ እዛም እዚህም ያሉት አሳቦች ሲታዩ ግን አብዛኛው ሰው ተስፋውን በዐቢይ ላይ የጣለ ይመስላል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የተግባቦት ወይም ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ደግሞ ሕዝቡ በግለሰቡ ላይ ያዘለውን ተስፈኝት የተቀበሉት አይመስልም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ዶክተር ዐቢይ ራሱን ሆኖ ወይስ የወከለውን ድርጅት ኢህአዲጋዊ አሳብ አዝሎ ይቀጥላል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲታይስ ህዝቡ ለዶክተር ዐቢይ እያሳየው ያለው ድጋፍ በሀገሪቱ ላይ ምን ዐይነት ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል የሚለው ሌላኛው ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡

ዶክተር ዐቢይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ….አቶ ደመቀ መኰነን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ዐዲስ አመራር ወደ መንበረ ሥልጣኑ ቢመጣ የተሻለ እንደሆነ በማሰብ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸውን የአማራ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ ዶክተር ደብረጽዮን ደግሞ ቀድሞውኑም ራሳቸውን ከውድድር ማውጣት ፈልገው እንደነበር ገልጸው….ሆኖም አካሄዱ እንደ ቀደመው እንደ ሥራ አስፈጻሚ፣እንደ ድርጅት በጋራ እንደሚሠሩ  ያላቸውን አስተያየት ከዋልታ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ የእነዚህ ሁለት ባለሥልጣናት ራስን ቀድሞ ከውድድሩ ማውጣት ላይ ያደረጓቸውን አሻሚ ንግግሮች ለጊዜው በዐቢይ አማካኝነት ሊመጣ የሚችል ፖለቲካዊ ለውጥ አለ ወይስ ሁሉም ባለበት ይቀጥላል የሚሉትን ደማና ያጠሉበታል፡፡

አሁን ህዝቡ ብቻ ሳይሆን የእነ ማክስ ዌበር መሰል ፍልስፋና የማይለቀው ኢህአዴግ ከቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ ጀምሮ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ፖለቲካዊ አካሄድ ድርጅቱን የት እንዳደረሰው ባለፉት ዓመታት ታይቷል፡፡ በፖለቲካ ርእዮት ዓለም የአንድ ድርጅት ፖለቲካዊ አመራርነት በግለሰቦች ላይ ትኩረት ሲያደርግ አንካሳነት ይበዛበታል፡፡ ድርጅቱ በተደጋጋሚ እያጋጠሙት ያሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሙስና በተለይም ደግሞ ኢህአዴግ አምኖና መርጦ ባስቀመጣቸው ከፍተኛ አመራሮች የሚደረግ ምዝበራ፣ የህዝቡ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች አለመከበር፣ የመረጃ ነጻነትና የመሳሰሉት…….ከአንድም ሁለቴ ኢህአዴግ ራሴን ፈትሸ በተሀድሶ እስተካከላለሁ እያለ ነገር ግን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ጥልቅ ተሀድሶው የት እንዳደረሰው በግልጽ ታይቷል፡፡

ስለዚህ ዐቢይ ገና በልጅነቱ ከኢህአዴግ ጋር እንደተዋወቀና በዚያው ሰብእና እንዳደገ ልዩ ልዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ዐቢይ ኢህአዴግ ቤት ማደጉ ሳይሆን ቁምነገሩ ሰውየው በትምህርትና በንባብ እንደ ግለሰብ የተሻለ ቁመና ያለው ሰው መሆኑ በሀገሪቱ ላይ ምን ዓይት ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም ከልጅነት ጀምሮ በኢህአዴግ ቤት ማደጉና አሁን ለደረሰበት አስተሳሰብ ወይም አብዮተኛነት የኢህአዴግ ድርጅት የደረሰበትን ፈተና ጠግኖ ሕዝቡ እንደሚፈልገው መሠታዊ ለውጦችን ያመጣል ወይስ እንደ ቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ ከሕዝብ ይልቅ ድርጅቱን ወደ ማዳን ያተኩራል የሚሉት ወሳኝ ኹነቶች ወይስ ወደ ፊት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ ላይ ደመናው አንዳንዣበበ ፈተና ይሆናል የሚለው ሌላኛው ጽንፍ ነው፡፡  በኢህአዴግ ቤት ራስን መሆን አይቻልም፤ ምን አልባት ከቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ውጭ ማለቴ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ዘወትር በንግግሩ ውስጥ “ድርጅቴ” የሚለው ወዶ አልበረም፡፡

በተለይ በማኅበራዊ መገናኛዘዴዎች ከሚንሸራሸሩት አሳቦች ተነሥተን አብዛኛው ሰው ዐቢይ በመመረጡ ለምን እንደመልካም አጋጣሚ መቀበል ፈለገ ስንል ምን አልባትም እንደ ግለሰብ ያለው በኢትዮጵያዊነት፣ በእኩልነት እንዲሁም ስለአመራርነት ያለው የተሻለ አተያይ ወይም ግንዛቤ ይመስለኛል፡፡ ይሄን ደግሞ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮች ያደረጋቸውን ንግግሮች መመልከት/ ማዳመጥ በቂ ነው፡፡    ስለዚህ ህዝቡ ዐቢይ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ሆኖ መመረጡን እያወቀ ነገር ግን ሰውየውን ከፓርቲው ነጥሎ ማየት መፈለጉ የዐቢይን ጉዞ  ምን መልክ ያስይዘዋል የሚለው ወሳኝ ፖለቲካዊ ትንታኔ ያስፈልገዋል፡፡

በእርግጥ በፖለቲካው መስክ የግለሰቦች ተራማጅነት ወደ ህዝብ ሲሸጋገር መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ በፖለቲከው ዘርፍ ያሉ ሙሁራን ይስማማሉ፡፡ ዐቢይ በዚህ ረገድ የተሻለ ግለሰባዊ አተያይ፣ ግለሰባዊ መረዳት፣ ግለሰባዊ የአመራር ዝግጁነት እንዳለው በተለያዩ መድረኮች ባደረጋቸው ንግግሮች፣ ሥልጠናዎች እንዲሁም ሙያዊ ሂሶች ተንጸባርቀዋል፡፡ ሆኖም እሱ እንደሚለው “ከላይ ስንሆን ከታች ያለን አመለካት ካልተስተካከለ” እንደ ድርጅት፣ እንደ ግለሰባዊ ተራማጅት ህዝቡ የሚፈልገውን ለወጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ በደቡብ አፍሪቃ  የአፓርታይድ ሥዓትን ለማስወገድ ብርቱ ጥረት ያደረገው ኔልሰን ማንዴላ እንደሚለው “ብዙ ጊዜ ከእኔ የላቀ ችሎታና አስተሳሰብ  ካላቸው ሰዎች ጋር ያደረኳቸው ውይይቶችና አሳቦች በሕይወቴ ጠቅመውኛል” እያለ ይናገራል፡፡

ዐቢይ ኢህአዴግ እስከ ዛሬ እንደ ባላጋራ ከሚያቸው ሙሁራን፣ የፖለቲካ ሰዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት ላይ ካላተኮረ ቅድመ ድቀቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡ አልፎ አልፎ ለይስሙላ ሲደረጉ እንደነበሩት ዐይነት ውይይቶች ሳይሆን ቀጣይነት ያለውና የዚህች ሀገር ሙሁራንና የፖለቲካ ሰዎች በሀገራቸው ጉዳይ ያገባኛል ብለው የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ካልተቻለ አሁንም ጉዙአችን አድካሚ ይሆናል፡፡ ባለፉት ጊዚያት እንደሆነው የፖለቲካ ሰዎች፣ ሙሁራን፣  ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ ከማድረግ ይልቅ አቅርቦ የመሥራት ልምድ ሩቅ ሳንሄድ ከጎረቤታችን ኬኒያ መማር እንችላላንና፡፡ ፖለቲከኛውም፣ ሙሁራኑም፣ ጋዜጠኞችም ሌላውም ሀገሩ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ስለኢትዮጵያ የምቆረቀረው፣ የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ ከሚል ደረመን መንጻት ካልቻለ ዐቢይ ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ ይሄ በዐቢይ ላይ ብቻ ሸክምን አራግፎ አንዳቺ ኹናቴ መጠበቅ የደወል ማንቂያ ነው፡፡ ዐቢይን በኢህአዴግ ውስጥ ማየትና ዐቢይ ኢህአዴግም ቢሆን እንደ ግለሰብ ተራማጅነት ማየት አለመቻል፤ ቀጣይ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ አለመረዳት ይመስለኛ፡፡

ዶክተር ዐቢይ ግለሰባዊ ተራማጅነቱን ይዞ እንደ ድርጅት ከሁሉም ጋር ከሠራ የዝህቡን ፍላጎት የማያሟለበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ድርጅታዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ለውጥ ይመጣል፡፡ ነገር ግን ፓርቲው እንደ ድርጅት ከተሀድሶው ሳይማር በአመራር ክፍተት ብቻ በሀሪቷ ላይ የተጋረጡትን ችግሮች እፈታለሁ ብሎ ከተነሣ አሁን መንታ መንገድ ላይ የቆመችው ኢትዮጵያ በዛው የመቀጠል እጣ ፈንታዋ ሰፊ ነው፡፡ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ ድርጅቱ እንደሚያምነው የአመራር ክፍተት ብቻ አይደለም ያለው፡፡  ቀደም ሲል በፓርቲው ውስጥ ተፈጥረው የነበሩ አለመግባባቶች፣ የጥልቅ ተሀድሶው ግምገማው ፍሬ አልባነት፣ የህዝብ ችግሮችን በተለይም ህዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሥር የሰደደ ሙስና፣ እንደ ዜጋ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል አለመታየት፤ የእኩል ተጠቃሚነት ችግርች፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ በተለያዩ ሕጎች ተጠርንፎ የታሠረው የመገናኛ ብዙኀን ነጻነት የሚሉት መሠረታዊ ለውጦችን የሚፈልጉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ስለዚህ ከላይ ባነሣናቸው መንደርደሪያ አሳቦች አማካኝት ዐቢይ ድርጅታዊ/መዋቅራዊ ወይስ ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል የሚለው ለዚች ሀገር መፍትሄ የቱ እንደ ሆነ በሚቀጥሉት ጊዚያት የሚታዩ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.