አድዋን በሲኒማ

0
526
picture by: Dawit Tibebu

የአድዋ ጦርነት በአገራችን ታሪክ በጣም ትልቅ ቦታ ያለው ጦርነት ቢሆንም፣ እስካሁን ግን ይህን ታላቅ ድል የሚዘክር ፊልም አለመሰራቱ በጣም ይገርመኛል። በተወሰነ መልኩ እስካሁን ድረስ አለመሰራቱ ጥሩ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ፣ ምክንያቴ ደግሞ የኢትዮጵያ የሲኒማ ኢንዱስትሪ በቂ አቅም አለው ብዬ ስለማላስብ ነው። እንደ አድዋ ያለ ትልቅ ታሪክ ፊልም ከተሰራለት ከፍተኛ ጥራት ባለው መልኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከመዝናኛነትም ባለፈ እንደማስተማርያነት እየተጠቀምንበት መተላለፍ መቻል አለበት ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ፊልም ሰሪዎች ይህን ለማድረግ የገንዘብ፣ የመሳርያ እንዲሁም የቴክኒክ አቅሙ የላቸውም። በዚህ ምክንያት ወደፊት በቂ አቅም ስናካብት ቢሰራ ጥሩ ነው እላለሁ።

picture by: Dawit Tibebu

 

አንድ ቀን ጊዜው ደርሶ ፊልሙ ሲሰራ የሚከተሉትን ወሳኝ ጉዳዮች ሊያካትት ይገባል ብዬ አስባለሁ፦

  1. አዲሲቷን ኢትዮጵያ ማስተባበር

በመጀመሪያ ከምንም ነገር በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አጼ ምኒሊክ በአዲስ መልክ የተዋቀረችውን፣ ብዙ አዳዲስ ብሄሮችን በውስጧ የያዘችውን ኢትዮጵያ እንዴት አስተባብረው ለድል ሊያበቋት እንደቻሉ ማሳየት ላይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሳቸውን ስልጣን ለመውሰድ(ለመቀማት) ያልሙ የነበሩ ነገስታትንም አስማምተው ከሳቸው ጎን ሆነው እንዲዋጉ ማሳመን ነበረባቸው። ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መሰጠት አለበት የምለው አሁን ሃገራችን እየተጓዘችበት ካለችው የመከፋፈል እና እርስ በእርስ የመጋጨት መንገድ እንድትመለስ የማንቂያ ደውል ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ብዬ ስለማምን ነው። በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የጥበብ ስራዎች ህዝብን አንድ ለማድረግ እና ለማስተባበር ሲጠቅሙ አይተናል። እንደ ቦብ ማርሌ ያሉ አርቲስቶች ድምጻቸውን ጥቁር ህዝቦች ለነጻነታቸው ለሚያደርጉት ትግል አበርክተዋል፣ከዛም በተጨ ማሪ በጃማይካ ውስጥ የነበረውን የእርስ በእርስ ግጭት ለማቆም እንደ“one love peace concert”ያሉ ዝግጅቶችን አዘጋጅተዋል። በጣልያን እንደ ጁሴ ፔማዚኒ ያሉ ጸሃፊዎች በጽሁፎቻቸው የሃገሪቱን ወጣት ለአንድነት እንዲነሳሳ ትልቅ አስተዋጽኦ ተጫውተዋል። በቅርቡም “BlackPanther”የተሰኘው ፊልም በአለም

ዙሪያ ያሉ ጥቁር ህዝቦችን በቆዳቸው ቀለም ኩራት እንዲሰማቸው እንዳደረገ አይተናል። እኛም ይህን ታላቅ ታሪካችንን በአግባቡ ከተጠቀምንበት አንድነታችንን የሚያጠናክር፣ በጋራ ስንሰራ ምን ማድረግ እንደምንችል የሚያሳይ የጥበብ ስራ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ ። እዚህ ጋር ግን ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር፣በጥንቃቄ እና ታሪካዊ እውነታውን በጠበቀ መልኩ ካልተሰራ ጭራሽ የባሰ መቃቃር ውስጥ ሊከተን እንደሚችል ነው።

  1. የቀደሙ ግንኙነቶች

ከዚህም በተጨማሪ መረሳት የለባቸውም ብዬ የማስባቸው ሌሎች ጉዳዮች አሉ።ከነዚህም አንዱ ንጉስ ምኒሊክ ከአጼ ዮሃንስ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እና በዚያን ጊዜ ከጣልያን ጋር የነበራቸው ስምምነት ነው። አጼ ዮሃንስ ንጉሰ ነገስት በነበሩባቸው ዘመናት ንጉስ ምኒሊክ ከጣልያን ጋር ከገቡባቸው ስምምነቶች አንዱ የሚከተለውን ይዘት ነበረው:የጣልያን ጦር ከአጼ ዮሃንስ ጦር ጋር ቢጋጭ ንጉስ ምኒሊክ ምንም አይነት እርዳታ ለአጼ ዮሃንስ ላይሰጡ ቃል ይገባሉ፣ ለዚህ ውለታቸውም  የጣልያን መንግስት የጦር መሳርያ ሊያበረክትላቸው ቃልይገባል።እንደዚህ ያሉ የቀደሙ ግንኙነቶችን ማወቅ እንዴት አጼ ምኒሊክ የንጉሰ ነገስትነቱን ዙፋን እንደተቀዳጁ እና በኋላም እንዴ ትጣልያን ወዳጅ መስላ ልትቀርባቸው እንደሞከረች ለመረዳት ይጠቅማሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላ ሊረሳ የማይገባው ነገር ለጦርነቱ መንስኤ የሆነው በጣልያንኛ እና በአማርኛ የተለያየ ትርጉም ያለው የውጫሌ ስምምነት ነው። በተለይም በስምምነቱ ውስጥ ካሉት ሃያ አንቀጾች ሁለቱን፣ማለትም አንቀጽ ሶስትን እና አንቀጽ አስራ ሰባትን በመጠቀም ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ የቅኝ ግዛት መረቧን እንዴት ልትጥል እንደሞከረች በደንብ ማስረዳት ይኖርበታል።

  1. የሴቶች አስተዋጽ

እስካሁን ለመዳሰስ የሞከርኩት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ያሉ ጉዳዮችን ነው፣ በጦርነቱ ጊዜ እና ከጦርነቱ በኋላ ከተከሰቱ ነገሮች ደግሞ የሚከተሉት የበለጠ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል እላለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ ሴቶች ለድሉ የነበራቸው ሚና በጉልህ መቅረብ(መታየት) መቻል አለበት። በዚህ ጦርነት  ላይሴቶች ስንቅ ከማቀበል ጀምሮ የቆሰሉ ወታደሮችን እስከማከም እንዲሁም በጦርሜዳው ላይ ከወንዶቹ እኩል እስከመዋጋት የላቀ አስተዋጽኦነበራቸው።እናም ይህ አስተዋጽኦ በደማቅ ሁኔታ(አገላለጽ) መቅረብ አለበት። ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት የንጉሰ ነገስቱ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ እና እሳቸው ይመሩት የነበረው ጦር ነው። ንግስቲቱ ወደ ጦርነቱ የራሳቸውን ጦር እየመሩ ከመሄዳቸውም ባሻገር ከሰላዮች መረጃ በመሰብሰብ እና በዚህ መረጃ መሰረት ንጉሱን ውሳኔ እንዲሰጡ ያግዟቸው ነበር። ራስመኮንን ጣልያኖችን መቀሌ ላይ በገጠሙበት ጊዜ ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ ውሃ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲዘጉት እና እጃቸውን እንኪሰጡ እንዲጠብቋቸው ያማከሯቸው እቴጌ ጣይቱ ነበሩ። ንግስቲቱ እንዲህ ያሉ ብልህ ውሳኔዎቻቸው ለኢትዮጵያውያን ድል ምን ያህል ወሳኝ እንደነበረ መዘንጋት የለበትም።

  1. በወቅቱ የነበረው የተፈጥሮ ችግር

ፊልሙ ብዙ ሰዎች ለሚያነሱት “ለምንድን ነው የኢትዮጵያ ጦር የጣልያንን ጦር እስከ ኤርትራ ድረስ ሄዶ ጠራርጎ ያላስወጣው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት መቻል አለበት። የዚህ ጥያቄ መልስ ሲጀመርም ጣልያን ኤርትራን ስትወር የኢትዮጵያ ነገስታት ለምን ማስቆም አልቻሉም ከሚለው ጥያቄ መልስ ጋር አንድ ነው። መልሱም በሃገሪቱ ውስጥ በወቅቱ ከባድ ድርቅ እና የከብት በሽታ መከሰቱ ነው። አድዋም ላይ በተደረገው ጦርነት ላይ ህዝቡ ይህን ችግር ከቤቱ አስቀምጦ የንጉሱን ጥሪ አክብሮ ነው ሊዋጋ የወጣው። ይህንን ሁኔታ ኪነ-ጥበባዊ በሆነ መልኩ መግለጽ ከተቻለ ለብዙ ሰዎች ጥያቄ የተወሰነ ማብራርያ መስጠት ይቻላል ብዬ አስባለሁ።

  1. የድሉ አለም አቀፋዊ ትርጉም

በመጨረሻም ይህ ፊልም የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ዙሪያ ላሉ ጥቁር ህዝቦች ምን አይነት ትርጉም እንደነበረው እና የተቀረው ዓለም ይህን የጥቁሮች ድል እንዴት እንዳየው በአጭሩ መዳሰስ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ።

መልካም መቶ ሃያ ሁለተኛ የአድዋ የድል በዓል ይሁንላችሁ። መጨመር ወይም መቀነስ አለበት የምትሉት ነገር ካለ ሃሳባችሁን በአስተያየት መስጫው ላይ ማስፈር ትችላላችሁ::

በኖኤል ምንዋጋው

 

 

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.