የሶርያ ከገነት ወደ ጃሃነም ጉዞ በሰባት አመታት ውስጥ

0
449

የእርስበርስ ውጊያው አሀዱ ከተባለ ሰባት አመታትን ሊደፍን ሁለት ወራት የማይሞላ ጊዜ ብቻ ይቀረዋል። ጦርነቱ በእስከዛሬ ጉዞው 500 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ሀገሩን ጥሎ ተሰዷል። ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ደግሞ ሀገሩን ሳይለቅ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ተፈናቅሎ ይገኛል። የእርስበርስ ፍልሚያው ተዋናዮች እልፍ ቁጥር ያላቸው ናቸው። ይህ የሶሪያ የእርስበርስ እልቂት ትንሹ መገለጫ ነው። ቀጣዩ ፅሁፍም ትኩረቱን በአለማችን አስፈሪ እልቂት ላይ አድርጎ ከሰሞኑ ልዕለ ሀያሏ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት በጦርነቱ ጣልቃገብነታቸውን ይበልጥ ለመጨመር ማቋዳቸው በፍልሚያው ቀጣይ ሂደት ላይ የሚኖረውን ጫና ከዚህ ቀደም የእልቂቱ ቆይታ ጋር አስተሳስሮ በዝርዝር ይቃኛል።

ለብዙ ጊዜያት የእርስበርስ ጦርነት አውድ የሚሰጠው የሶሪያው እልቂት ከመነሻ አላማው ተቀይሮ ሌላ ቅርፅ ከያዘ ዋል አደር ብሏል። የአረባዊቷ ምድር ሶሪያ የአለም ታላላቅ ሀይላት፣ የቀጠናው ጎረቤቶቿ እና የተለያዩ የዘርና ሀይማኖት ቡድኖች የፍልሚያ ቦታ ከሆነች ሰንብታለች። ከሰሞኑ ደግሞ አሜሪካ በጦርነቱ ያላትን ሚና ለመጨመር ማሰቧን በግልፅ አስታውቃለች። ይህ የልዕለ ሀያሏ እቅድም በጦርነቱ ቀጣይ ጉዞ ላይ ተጨማሪ አቀጣጣይ ቤንዚን ሆኖ እንዳይመጣ ያሰጋል። ከአሜሪካ በተጨማረ ደግሞ ሌሎች በጦርነቱ ላይ አሻራቸውን ሲያሳርፉ የቆዩ ሀገራት በምድረ ሶሪያ ያላቸውን ጣልቃገብነት ሊያስፋፉ እየተሰናዱ መሆኑ ጦርነቱን ለአዲስ እና ይበልጥ ለከበደ ቀጣይ ሂደት እንዳያበቃው ይበልጥ አስፈርቷል።

በሶሪያ እየተደረገ ያለው ፍልሚያ እስካሁን ንፁህ አሸናፊዎቹን መለየት አልቻለ ይሆናል ተሸናፊዎቹ ግን ታውቀዋል። ተሸናፊዎቹ ከዕለት ዕለት በሀገራቸው እና በስደት እየተሰቃዩ ያሉት ብዙ ሚሊዮን ሶሪያውያን ናቸው። ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ በሰሜን እና ምዕራብ ኢድሊብ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎች የሩሲያና የሶሪያ መንግስት የአየር ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። ከጥቃቱ ጋር በተያያዘም ብዙዎቹ ለሁለተኛና ሶስተኛ ጊዜ ለመፈናቀል ተገደዋል። በሰሞነኛው ጥቃትም በአጠቃላይ ከ 200,000 በላይ ሰዎች የነበሩበትን ስፍራ ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል። የእርዳታ ድርጅቶች እና የፓለቲካ አቀንቃኞች እንደሚናገሩት ከሆነ በሶሪያ አሁንም ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች   ተደጋጋሚ የጥቃት ኢላማ መሆናቸው ቀጥሏል። መሰረታዊ የእርዳታ አቅርቦት መገታትም ትልቅ የቀውሱ ፈተና እንደሆነ ይገኛል።

በተደጋጋሚ ማነው ለሶሪያ ቀውስ ተጠያቂ? የሚል ጥያቄ ሲነሳ ይደመጣል። ለጥያቄው አጭሩ መልስ በአብዛኛው ሁሉም አካላት የሚል ነው። በእርግጥ እንደ ቭላድሚር ፑቲን አይነቶቹ አካላት ለቀውሱ ትልቅ ሚና ሲሰጣቸው ይታያል። በዚህ ረገድ የሩሲያው መሪ አሳድን ለመደገፍ እና ሀገራቸው በሜድትራኒያን ያላትን ስትራቴጂክ ቦታ ለማስጠበቅ ጣልቃ ከገቡበት 2015 አንስቶ በትልቁ ሲወቀሱ ቆይተዋል። ፑቲን በመንግስት ተቃዋሚዎች በተያዙ ስፍራዎች እና በከተሞች እንዲደረግ የሚያዙት የአየር ጥቃትም በዋነኛ ተወቃሽነት የሚያስነሳቸው ተግባር ሆኖ እንደቀጠለም ነው።

በ 2016 የአሊፓን ከተማ ከተቃዋሚ ሀይሎች ለመንጠቅ የሶሪያ መንግስት በተጠቀመው ህገወጥ ኬሚካል ሩሲያ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናት። ከሁለት አመታት በፊት በተፈፀመው ተግባርም ፑቲን እንደአሳድ ሁሉ በጦር ወንጀል ፈፃሚነት ሊታዩ እንደሚገባ የሚጠይቁ አካላት አሉ። በሌላ በኩል ግን ሁሉንም ጥፋት በሩሲያና አሳድ ላይ ማላከክ ተገቢ እንዳልሆነ ይገለፃል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ኢድሊብ በምሳሌነት ትጠቀሳለች። ከተማዋ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው ባለ 14,000 ጦሩ ሀያት ጣህሪር አልሻም የተሰኘው የእስላማዊ ቡድን መናኻሪያ ናት።

ይህ የእስላማዊው ቡድን በከተማው መገኘትም ትልቅ ችግርን አስከትሏል። ምክንያቱም እንደ አይኤስ ሁሉ ቡድኑ በሶሪያን እስላማዊ መንግስትን ለመመስረት ይንቀሳቀሳል። ይህ እንቅስቃሴም በከተማዋ ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን በከባድ ችግር ውስጥ ከቷቸዋል። ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ የሶሪያ መንግስት በጂሀዲስቶች ላይ አንድ መንገድ እየተከተለ ይገኛል። ይኸውም የአቅርቦት መንገዳቸውን በመዝጋት እና አማራጭ በማሳጣት እጅ እንዲሰጡ የማድረግ ነው። ነገርግን ከዚህ ቀደም በራቃ አሁን ደግሞ በኢድሊብ የሚገኙ ሀይላት በህፃናት፣ በአቅመ ደካሞች ሽፋን መንቀሳቀስን ስራቸው አድርገው ይዘውታል። እነዚህን ሀይላት ለማጥቃት የሚመጡ የአሳድ የጦር አውሮፕላኖች የሚሰነዝሩት ጥቃት ገፈት ቀማሽም ሰላማዊው የሶሪያ ህዝብ ነው። የሰቆቃው ሌላኛው የወቀሳ ማረፊያ ደግሞ የአሳድ ተቃዋሚዎች አንድ የተጠናከረ ስብስብ ሆነው መውጣት አለመቻላቸው ነው። ነገርግን የዚህ የቡድኖቹ መከፋፈል እና ልዩነት የሚገልፀው ሌላ ምልከታ አለ። ይህም ለቡድኖቹ መከፋፈል ምክንያቱ በሶሪያ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ሀይላት የሚጋጭ አቋም ባላቸው በኢራን፣ ቱርክ፣ ሳውዲ አረቢያ ወይም ኳታር ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ መሆኑ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም እያንዳንዱ ጎረቤት ሀገር አላማውን የሚያስፈፅምለትን ቡድን በአምሳያው ቀርፆ ድጋፍ እየሰጠ ያንቀሳቅሳል።

በምዕራባውያን የሚደገፈው የነፃ ሶሪያ ወታደራዊ ቡድንም በውጪ ሀገራት ከሚረዱ ሀይላት አንዱ ነው። የቡድኑ አባላትም ከትራምፕ አስተዳደር እርዳታ ለመጠየቅ ባሳለፍነው ሳምንት በዋሽንግተን ከትመው ነበር። ነገርግን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሬክ ቴለርሰን በካሊፎርኒያ በሰጡት መግለጫ የትራምፕ አስተዳደር ኢላማ ኢራንን ከሂደቷ ማስቆምና በሶሪያ የሚገኘውን የአልቃይዳ ሀይል ማኮላሸት መሆኑን በግልፅ ተናግረዋል። የቴለርሰን ንግግርም የትራምፕ አስተዳደር በዚህ ሰዓት የሶሪያ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲገኝለት እና የድህረ አሳድ እንቅስቃሴ እንዲጀመር መስራት ላይ ትኩረቱ እንዳልሰጠ ያሳየ ተብሎለታል። በጦርነቱ ትልቅ ሚና ያላት ሌላኛ ሀገር ቱርክ ናት። ከሶሪያ የሚሰደዱ ስደተኞችን በመቀበል ቀዳሚ ሆኖ የቆየችው የስደተኞች መናኻሪያዋ ከአመታት በኋላ አቋሟን ቀይራ ተገኝታለች። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጠይብ ኤርዶጋን እንዳሉት ሀገራቸው በሶሪያ ያላት አቋም ቀንሶ የሶሪያን ኩርድ መደምሰስ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

ለኤርዶጋን ቱርካዊም፣ ኢራቃዊም ሆኑ ሶሪያዊ ሁሉም ኩርዶች አሸባሪ ናቸው። በቀጣይም ፕሬዝዳንቱ ኤድሊብ ከተማ አቅራቢያ ያለችውን አፍሪንን እንደሚወሩም አስፈራርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሶሪያ ኩርድ ሚሊሻዎችን የምትረዳውን አሜሪካ እየወቀሱ ይገኛል። የአሳድ መንግስት እንደሚለው ከሆነም ቱርክ በጦርነቱ ያላትን ጣልቃገብነት የምትጨምር ከሆነ የኩርድ ሀይል ይዳከማል። የሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት ተወቃሾች ዝርዝር በዚህ የሚያበቃ አይደለም። በሶሪያ ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት ለምን ደካማና ውጤት አልባ ሆነ? የሚለው ጥያቄ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት የቀድሞው የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴቪድ ሚልባንድ እንደገለፁት ከሆነ ብሪታኒያ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል እንደመሆኗ በእርስበርስ ጦርነቱ በትልቁ ተሳታፊ እና መፍትሄ ፈላጊ መሆን አለባት ብለዋል። በተያያዘ መልኩ እልቂቱ ከሚያስከትለው ተጨማሪ ስደተኞች አንፃር ተጎጂው የአውሮፓ ህብረትስ ምን እየሰራ ይሆን? የሶሪያ የሰላም ስምምነት ጉዳይስ ከምን ላይ ነው? የሚለው ነገር በብዙዎች እየተነሳ ያለ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ውይይቶች በተባበሩት መንግስታት መሪነት በዚህ ሳምንት እንደሚቀጥሉ ተነግሯል። ነገርግን የሚደረጉት ውይይቶች ለሶሪያ ቀውስ መፍትሄ የማምጣታቸው እድላቸው ዜሮ ወይም ምንም እንደሆነ እየተገለፀ ይገኛል። በሌላ በኩል የኢራን አብዮታዊ ጠባቂዎች እና የሺአ ቅጥረኞች ከጦርነቱ አትራፊ ለመሆን ሁሉንም አማራጮች እየተጠቀሙ ነው። ፑቲን ከአጋሮቻቸው ቴህራን እና ቱርክ ጋር በማበር አሳድን በስልጣን ለማቆየት የእርስበርስ ፍልሚያውን እያቀጣጠሉ ናቸው።

በምዕራቡ አለም የሚገኙ ብዙዎች ለቀውሱ መፍትሄ አለማግኘት አሜሪካንን ከየትኛውም አካል በበለጠ ሲተቹ ቆይተዋል። ለትችታቸው ማጠናከሪያነትም የኦባማ አስተዳደር በአካባቢው የመሪነት ሚና የሌለው እንደነበር እና ትራምፕ ከፑቲን ጋር አላቸው የሚሉትን ድብቅ ግንኙነት እንደ ምክንያት ሲያነሱ ታይተዋል። ይህ ሁኔታ ግን በ 2018 እንደማይቀጥል እየተነገረ ይገኛል። ቲለርሰን በሰሞነኛ መግለጫቸውም በጦርነቱ አሜሪካ በሚኖራት ጣልቃገብነት ላይ ክፍተት ያለው የወታደራዊ ታማኝነት እንደሚኖር አመልክተዋል። በዚህም ተባለ በዚያ ግን በሶሪያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ በቶሎ መስተካከል ካልቻለ እንደቴለርሰን መግለጫ ከሆነ ቀጣዩ ሂደት ይበልጥ አስከፊ ነው። እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውስጠ ወይራ አስተያየት ከሆነ መፍትሔ በቶሎ ካልተገኘ ሶሪያ ህዝቦቿ በስደት አልቀው አሜሪካ እና ከኢራን እንዲሁም እስራኤል፣ ሳውዲ፣ ኳታር፣ ሂዝቦላ፣ ሀማስ፣ ፑቲን፣ አሳድ፣ ኤርዶጋን፣ አልቃይዳ እና ኩርዶች ከዳር ሆነው የሚታኮሱባት ሰው አልባ መሬት መሆኗ አይቀሬ ይመስላል።

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.