አቡበከር አልባግዳዲ በአለም ቁጥር አንዱ ተፈላጊ- ከቻላችሁ ያዙኝ

0
288

በሚኪያስ በቀለ

ቀንም ማታም ላለፉት ሶስት አመታት ስፍር ቁጥር ያሌላቸው የአለም ሰላዮች እሱን ፍለጋ ይኳትናሉ። እዚህ ነው ሲባል እዛ እያለ አሻራው የማይገኝ ጥላ ቢስ እንደሆነ ቀጥሏል። እሱን ለያዘ ወይም ያለበትን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር ተዘጋጅቶለታል። መገኛው ብቻ ሳይሆን የግል ህይወቱም የሚጨበጥ ማስረጃ የሌለው መንፈስ የሚባል አይነት ነው፡፡ ሰውየው ኢብራሂም አዋድ ኢብራሂም አሊ ሞሀመድ አል ባድሪ አል ሳምሪ በሚለው ሙሉ ስሙ ወይም ብዙዎች በሚያውቁት የተለመደ ስያሜው አል ባግዳዲ ተብሎ ይጠራል። ይህ አለም በዘመኗ አይታው የማታውቀውን ጭካኔ ያሳያትን አይኤስ የተሰኘ የሽብር ቡድን እየመራ የአይጥ ድመት ጨዋታን ላለፉት አመታት እየተገበረ ያለው ኢራቃዊ ሰው የዛሬው ትኩረት ማረፊያ ነው።

ከአለም ቁጥር አንድ ተፈላጊው ሰው ይፋዊ የትምህርት መዝገቡ የተገኘው መረጃ በ 1991 በከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱ በተፈተነው የመውጫ ፈተና ከ 600 ነጥብ 481 ማስመዝገብ የቻለ የተባ ማሰላሰያ የነበረው ባለብሩህ አዕምሮ ተማሪ እንደነበር ያረጋግጥልና።

ነገርግን ያገኘው ነጥብ የሚፈልጋቸውን ትምህርት ክፍሎች ለመቀላቀል ሳያስችለው ቀረ። በዚህም የተነሳ ይወዳቸው ከነበሩ የህግ፣ የሳይንስ ነክ መምህርነት እና የቋንቋ ትምህርት ክፍል ተሰናከለ። እንዳሰበውም እግሩ የባግዳድ ዩንቨርስቲን መርገጥ ሳይችል ቀረ።

በሌላ በኩል ደግሞ አይኑ ከሩቅ መመልከት ላይ ደካማ የነበረ በመሆኑ ለኢራቅ ወታደራዊ አገልግሎት ብቁ ከመሆን አገደው። ቢሆንም ግን ወድቆ ከመቅረት የሚገላግለው አንድ የመጨረሻ እድልን አገኘ። በዚህ ምክንያትም ኢራቅ ዩንቨርስቲ የሚሰኘውን የሀይማኖት ትምህርቶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ተቋም መቀላቀል ቻለ። በእዛም የእስልምና ህግ እና ቁራንን በሚገባ ማጥናት ቻለ።

በ 2014 የወጣ የአሜሪካና የኢራቅ የስለላ ተቋም ትንተና ደግሞ በእስልምና ትምህርት ከሳዳም ዩንቨርስቲ መመረቁን ያትታል። ከዚህ በተቃራኒው በአክራሪ ሀይሎች የመረጃ ቋት ላይ ይፋ የተደረገ መረጃ በእስልምና ጥናት ትምህርት የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪን እንዳገኘ ያትታል።

አልባግዳዲ ባለፉት 18 ወራት በአንድ ስፍራ ላይ እንደሚገኝ ተደርሶበት የነበረ ቢሆንም በአጋጣሚ ሊያመልጥ ችሏል። የአይኤሱ መሪ በድንገት ኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች ለመጠቀም ከመሞከሩ ጋር በተያያዘ አጋጣሚው በአጥብቆ ፈላጊው አሜሪካ እጅ ሊያስገባው ተቃርቦ ነበር።

በመጀመሪያው አጋጣሚ ህዳር 3፣ 2016 ላይ የኢራቅ እና የኩርድ ሀይላት ሞሱልን ለመያዝ ሲገሰግሱ አልባግዳዲ የ 45 ሰከንድ ስህተትን ሰራ። ተፈላጊው ሰው ከሞሱል በምዕራብ አቅጣጫ እና በታል አፋር ከተማ መሀከል ላይ የእጅ ስልክ በማንሳት ማውራት ጀመረ። እሱ ካለበት ትንሽ ፈቀቅ ብለው የነበሩት ፈላጊዎቹም ለተከታዮቹ ያሉበትን ቦታ ለጠላት አሳልፈው እንዳይሰጡ የሚሰብከውን የአልባግዳዲ የተለየ ድምፅ ሰምተው ተደነቁ።

ነገርግን ለ 45 ሰከንድ እንደተነጋገረ ጠባቂዎቹ በመምጣት ስልኩን ተቀብለው ከአደጋ አትርፈው አስመለጡት። ያ የአልባግዳዲ እንዝላል ድርጊትም የአልባግዳዲ ፈላጊዎች ሰውየውን አድነው ለመያዝ መጠነኛ እድልን የፈጠረላቸው አጋጣሚ ነበር።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመትም በድጋሚ በእንዝላልነት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ሲጠቀም በስለላ ቅኝት ውስጥ ገባ። አልባግዳዲ ባጃ በተሰኘችው የአይኤስ መናኻሪያ ከተማ ያደረገው የስልክ ግንኙነት የድረገፅና የስልክ መሳሪያዎችን ሰብረው በሚገቡ የስለላ ኢላማዎች ውስጥ እንዲገባ አደረገው።

ነገርግን ክስተቱ በጣም የፈጠነ ስለነበር ወደኢላማ ቦታው የተዋጊ ጀቶችን መላክ ሳይቻል ቀረ። ከዚህ በተጨማሪም በትክክል የት እንደተደበቀ ማወቅ ከባድ ነበረ። አልባግዳዲ በዙሪያው ያሉት ጠንካራና ንቁ ጠባቂዎች ህይወቱ እንዲቆይ ትልቅ እገዛን አድርገውለታል።

በአይኤስ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው በሚፅፏቸው ፅሁፎች የሚታወቁት ኢራቃዊው ምሁር ሂሻም አልሀሺሚ እንደሚሉት ከሆነ አልባግዲዲ ከሽብር ቡድኑ መስራች ግለሰቦች በህይወት መቆየት የቻለ የመጨረሻው ሰው ነው። አይኤስ በምስረታው ከነበሩት 43 ዋነኛ መሪዎች መትረፍ የቻለው እሱ ብቻ ነው።

ቡድኑ በጨቅላ እድሜው ከነበሩት 79 ከፍተኛ አመራሮች በህይወት የሚገኙት 10 ብቻ ናቸው። በቡድኑ የነበሩት 124 የመካከለኛ ደረጃ አመራሮች በተለያየ ጊዜ የስልጣን ደረጃቸውና ምድብ ቦታቸው ሲቀያየር ቆይቷል። በእያንዳንዱ ስድስት ወራትም ወይ ተገለዋል ወይ ከስልጣን ቦታቸው ተነስተው በሌላ ተተክተዋል። ኤልባግዳዲ ግን የሚዘረጋበትን የስለላ መረብ እየበጣጠሰ አሁንም የቀደመ ቦታው ላይ ይገኛል።

በ 1971 አልቡ ባድሪ ከተሰኘው ጎሳ በኢራቋ ሳማር የተወለደው አልባግዳዲ ቤተሰቡ ከነበረው አራት ወንድ ልጆች ሶስተኛው ነው። ከእሱ ጋር ቅርበት ያላቸው እንደተናገሩለት ተፈላጊው ሰው በወጣትነቱ ብጥብጥን የሚጠላ አይናፋር እና ሰውን የሚስብ ነገር የሌለው ጭምት የሀይማኖት አዋቂ ነበር።

የአለም ቁጥር አንድ የጊዜያችን ተፈላጊ ሰው ከአንድ አስርት አመታት ለሚበልጥ ጊዜም ከባግዳድ በስተምዕራብ አቅጣጫ ከሚገኘው ቶብቺ መስኪድ ጋር ጎንለጎን በነበረ ቤት ውስጥ ብቻውን እስከ 2004 ኖሯል። በአንድ ወቅት የኢራቅ እስላማዊ ቡድን መሪ አህመድ አልዳባሽ አልባግዳዲን በሚመለከት ከቶብቺ ነዋሪዎች ጋር የሚመሳሰል አስተያየትን መስጠቱ ይጠቀሳል።

አህመድ ሰውየውን ሲገልጸፀው “በእስልምና ዩንቨርስቲ ውስጥ ከእሱ ጋር ነበርኩ። አንድ አይነት ትምህርት የምንማር ቢሆንም ጓደኛዬ አልነበረም። ጊዜውን ለብቻው የሚያሳልፍ ዝምተኛ ሰው ነበር። ሁሉንም የተዋጊ ሀይላት መሪዎች በግል ደረጃ አውቃቸዋለሁ።

“የቀድሞው የአልቃይዳ መሪ አልዛርቃዊ ለእኔ ከወንድም በላይ ቅርበት ነበረው። አልባግዳዲን ግን በቅርበት አላውቀውም። እሱ ብዙም ጥቅም ያለው ተደርጎ የሚታይ አልነበረም። በነበርኩበት ስፍራ ፀሎት ይመራ ነበር። እሱን ማንም ትኩረት አይሰጠውም ነበር።” ይላል።

የፀጥታ አማካሪ ድርጅት የሆነው ሶፋን ግሩፑ ተንታኝ ፓትሪክ ስኪነር በበኩላቸው የአሜሪካና ኢራቅ መንግስታት አልባግዳዲን በአካል ቢያውቁትም ያለፈ ህይወቱ በእርግጠኝነት የማይታወቅ እና የአፈታሪክ አይነት ቅርፅ ያለው እንደሆነ ይገልፃሉ።

እዚህ ላይ በተፈላጊው ሰው ዙሪያ የሚሰጡ ምስክርነቶች በሙሉ ልክ ለመሆን የቀረቡ እንደሆኑ እንድናምን የምንገደድበትን አንድ ነገር እናገኛለን። ይኸውም “የማይታየው ሼሂ” የሚለው ተቀፅላ ያለው ስሙ ነው። ሌላኛው አስገራሚ ነገር ደግሞ አልባግዳዲ የቀድሞ ታሪኩ ብቻ ሳይሆን የአሁን ሁኔታውም ከቀደመው ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ነው።

የአለም ቁጥር አንድ ተፈላጊው ሰው ለሽብር ቡድኑ አባላት ንግግር በሚያደርግበት ጊዜ በሙሉ መድረክ ላይ የሚወጣው ፊቱን በሰው ሰራሽ ፊት ወይም ማስክ ሸፍኖ ነው። በተያያዘ መልኩ የሽብር እንቅስቃሴ ሂደቱም የአልባግዳዲ ህይወት ግልፅ ያልወጣና ድብቅ እንደሆነ ማሳያ ነው።

አንዳንዶች አልባግዳዲ በሳዳም ዘመነ መንግስት የእስላማዊ አብዮተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ። ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ ከዚህ የሚጣረስ ነገር ይናገራሉ። የመረጃው ምንጮች በ 2003 አሜሪካ ኢራቅን ስትወር ከአብዮተኛ ይልቅ የመስኪድ ሀላፊ እንደነበር ያወሳሉ።

ከኢራቅ ወረራ በኋላም አልባግዳዲ ጀማት ጃይሽ አህል አል ሱና ዋል ጀማህ የተሰኘው ወታደራዊ ቡድን እንዲቋቋም እገዛ እንዳደረገ በህይወቱ ዙሪያ የተፃፉ ድርሳናት ያወሳሉ። ከዛም እሱና ቡድኑ ሙሀጂዲን ሹራ ምክር ቤት የተሰኘውን ስብስብ ተቀላቀሉ።

ስብስቡ ስሙን ወደ ኢራቅ እስላማዊ ቡድንነት ሲቀይርም አልባግዳዲ የቡድኑን ከፍተኛ ቦታ ማግኘት ችሏል። በአይኤስ ሽብርተኛ ቡድን እድገትና ውድቀት ውስጥም የአልባግዳዲ ህይወት ብቻ ሳይሆን ሞቱም አከራካሪ እንደሆነ የቀጠለ ነው።

አልባግዳዲ በተለያየ ጊዜ ህይወቱ እንዳለፈ ሲነገር ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪም የአልባግዳዲ ህይወት ማለፍ በሽብርተኛ ቡድኑ ቀጣይ እጣፈንታ ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚለው አከራካሪ እንደሆነ ያለ ወቅታዊ ጉዳይ ነው። በዚህ ዙሪያም ትልቅ አመኔታን ያገኘ አንድ ሀሳብ አለ።

ይኸውም የአልባግዳዲ መሞት በቡድኑ ቀጣይ እጣፈንታ ላይ ተፅዕኖ እንደሌለው የሚገልፅ ነው። ለሀሳቡ መደገፊያ እንዲሆን በማሰብም ቡድኑ ለሚያደርሰው ጥቃትና እቅድ እየሰሩ ያሉ ዋነኛ ሀይላት በሌሎች ሀገሮች እንደሚገኙ የሚያወሳ አመክኖ ይነሳል።  በሂደቱም አቡ በከር እና አልጆቢር የሚሰኙ ሁለት ሰዎች ትልቅ ሚናን እየተወጡ እንደሆነ ታውቋል።

ሽብርተኞችን የመመልመል፣ የማስታጠቅ እና ተዋጊዎችንና አስፈላጊ ነገሮችን ወደተፈለገው የጥቃት ቦታ የማጓጓዝ ስራ የሚመራው በእነሱ ነው። በአለም ዙሪያ የሽብር ቡድኑ ካለው 35 ቅርንጫፍ 33 ያህሉ በሁለቱ ሰዎች የሚዘወር ነው። አንዱ በቱርክ ሌላኛው በስካንድኒቪያ ሀገራት እንደሚገኙም ይነገራል።

በሌላ በኩል የሽብር ቡድኑ አሜሪካ በአየር ጥቃት እንጂ መሬት ወርዳ እንደማትዋጋው ትልቅ እምነት ማሳደሩ ይወሳል። ይህ ሁኔታም በፖለቲካ ተንታኞች ቡድኑ ከአሜሪካና አጋሮቿ ጋር እያደረገ ባለው ውጊያ ድል እንደሚያስመዘግብ እንዲያስብ እያደረገው እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል። በዚህ ተባለ በዚያ ግን አልባግዳዲ አሜሪካና አጋሮቿ በጥብቅ የሚፈልጉት ቀዳሚ ጠላታቸው ሆኖ ቀጥሏል።

በኢራቅና አውሮፓ ሰላዮች ዘንድ አጥብቆ የሚፈለገው ሰው ባለፉት 18 ወራት ባጅ በተሰኘው ሰፈር መክተሙ ይታመናል። ከዚህ በተጨማሪም በባጅ ቆይታው በድንበር ከተማዋ አቡ ከማል እና ከሞሱል በስተደቡብ ባለችው ሺርካት ከተማ መሀከል ባለመጠነኛ ቦታ እንቅስቃሴ ማድረጉ ተነግሯል።

አልባግዳዲ በ 2015 በተደረገ የአየር ጥቃት ክፉኛ መጎዳቱን የስለላ ተቋማት ማረጋገጣቸውም አይረሳም። ከዛ በኃላ በነበረው ጊዜም ባጅ መንደር ተቀምጦ ከጉዳቱ ለማገገም ጥረት ማድረጉን አንዳንድ ውስጥ አዋቂ ምንጮች አረጋግጠዋል።

አሁንም ግን በደረሰበት ጉዳት ምክንያት እንቅስቃሴው የተገደበ መሆኑ ይነገራል። ከረመዳን ፆም በኋላ በአቡ ከማል ከተማ እንደተመለከተው የተናገረ አንድ እማኝ አልባግዳዲ ገፅታው በድካም ዳምኖና በራስ መተማመን መንፈሱ ጨልሞ እንደተመለከተ ገልጿል።

የአሜሪካ መንግስት በወታደራዊ ቅኝት ባደረገው አሰሳ ተፈላጊው ሰው ከሶሪያ ጋር በሚዋሰነው የኤፍራጠስ ሸለቆ እንደሚገኝ ግምቱን አስቀምጧል። በሌላ በኩል ግን የአካባቢው ባለስልጣናት አልባግዳዲ በታርታር ሰርጥ እና በረሀ ወደሚገኝ ቦታ እንዳመራ ይናገራሉ።

እዚህ ላይ ግን መገንዘብ ያለብን ነገር ሁለቱም አካላት ሞራሉ እየተንኮታኮተ ያለው መሪና የሽብር ቡድኑ ወደመጨረሻው መጀመሪያ መቃረባቸውን የሚገልፅ ተመሳሳይ አቋም መያዛቸው መታወቁን ነው።

ስለሁኔታው የተናገሩ አንድ አካባቢው ባለስልጣንም “እሱ ማሳረጊያው ወቅት ላይ ይገኛል። በመጨረሻም በዚህ ዓመት ላይ እናድነዋለን!” ሲሉ በራስ መተማመን መንፈስ ተናግረዋል።

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.