በሚኪያስ በቀለ

ከ 16 አመታት በላይን የፈጀ ጦርነት ነው። ከ 2,300 በላይ ወታደሮች ተሰውተውበት ከ 750 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ገንዘብ ፈሶበታል። ይህ የአፍጋኒስታን ያለፉት አመታት ቁንፅል ታሪክ ነው። አሜሪካ ለአመታት ከ 100 ሺህ በላይ ወታደሮችን ልካ በአፍጋኒስታን ያደረገችው ጦርነት በሽንፈት ተጠናቋል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ጦርነቱስ የአለም ድሀዋን ሀገርም ለምን ማረጋጋት ሳይችል ቀረ? በቀጣዩ ዘገባ ጉዳዩን በስፋት ይዳስሳል።

የአሜሪካ የአፍጋኒስታን የውድቀት ታሪክ ሮዝ ቀለም ባለው ኦፒየም በተሰኘ አደንዛዥ እፅ ላይ ያተኩራል። አሜሪካን በአፍጋኒስታን የነበራት ቆይታ በማዕከላዊ እስያ ያላትን ህገወጥ የኦፒየም ንግድ መቆጣጠር ስትችል የሚበረታ መቆጣጠር ሲያቅታት ደግሞ የሚያጎመራ ሆኖ አመታትን አሳልፏል።

ከ 2001 ጥቅምት አንስቶ አፍጋኒስታንን ከታሊባን ርዝራዦች የማፅዳትና የመቀየር ዘመቻው በሀገሪቱ በተፈጠረው የተትረፈረፈ የሄሮይን ንግድ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። የሀገሪቱ የኦፒየም ምርት በ 2001 ከነበረበት 180 ቶንስ በአመቱ የብዙ እጥፍ ጭማሪ አምጥቶ 3,000 ደረሰ። በ 2007 ደግሞ ቁጥሩ ወደ 8,000 አሻቀበ።. በየአመቱ ፀደይ ወራት ላይም የኦፒየም እርሻው አዳዲስ የታሊባን ጉሬላ ተዋጊዎች መፈልፈያ ምክንያት ሆነ።

አሜሪካ ባለፉት 40 አመታት በአፍጋኒስታን እጇን ባስገባችበት እያንዳንዱ ቆይታ ሁሉ ኦፒየም እጁ አለበት። የ 1980ዎቹ ድብቅ ጦርነት፣ የ 1990ቹ የርስበርስ ጦርነት ከ 2001 ወረራ በኋላም አደንዛዥ ዕፁ የሀገሪተን ቀጣይ እጣፈንታ በመወሰን በኩል ቀዳሚ ሚና ነበረው። እዚህ ላይ አንድ የሚደጋገም ምፅት ያለው ቀልድ አለ። ይህም የአፍጋኒስታንን የተለየ የብዝሀ ሀብት በአሜሪካ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ይችን አለም ጥግ ላይ የምትገኝ ወደብ አልባ ሀገር ላይ ህገወጥ የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠር አድርጎ የፖለቲካ እድሏን መወሰን እና የውጪ ጣልቃ ገብነትን ማመቻቸት የሚል።

በ 1980ዎቹ  ከሶቪየት የአፍጋኒስታን ወረራ ጋር በተያያዘ የነበረው የሲአይኤ የድብቅ ጦርነት በአፍጋኒ ፓኪስታን ድንበር ላይ ለተቀጣጠለው የሄሮይን ንግድ መነሻ ነው። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ 1986 “በዳርቻ የሀገሪቱ ክፍሎች የፖሊስ ሀይል የለም። ፍርድ ቤት የለም። የግብር አሰራር የለም። ህገወጥ መሳሪያም አይታይም። ሀሺሽና ኦፒየም ብዙውን ጊዜ ይታያሉ።” የሚል መግለጫን አውጥቶ ነበር።
በወቅቱ የሶቭየት ሀይልን ለመዋጋት አሜሪካ ያቋቃመችው የጉሬላ ተዋጊ እንቅስቃሴም እጁን አርዝሞ ትልቅ መዘዝ አስከተለ። ሲአይኤ የራሱን ተዋጊ ሀይል ጥምረት ከመፍጠር ይልቅም ከቅርብ ጊዜ በኋላ የድንበር ተሻጋሪ የኦፒየም ንግድ ላይ ቁልፍ ሚና መወጣት በጀመረው ጠንካራ የፓኪስታን የስለላ ተቋም ላይ ተንተርሶ መንቀሳቀስ ጀመረ።

የአፍጋኒስታን የኦፒየም ምርት በአመት ከነበረበት እየጨመረ በሄደበት ወቅትም ነገሩን የሚመለከተው በሌላ አቅጣጫ ነበር። የሲአይኤ የአፍጋኒስታን የድብቅ ዘመቻ በጀመረበት 1979 እና 1980 በአፍጋኒ ፓኪስታን ድንበር የሄሮይን ቤተሙከራ የሚከፈትበት ጊዜ ነበር። በጥቂት ጊዜ ውስጥም ነገሩ ገዝፎ በ 1984 አፍጋኒስታን በአሜሪካ ካለው የሄሮይን ንግድ 60 በመቶውን እንድትቆጣጠር አስቻላት። በተመሳሳይ ወቅት ከአውሮፓ ገበያ 80 በመቶው በአፍጋኒስታን ሄሮይን ምርት የተያዘ ነበር።
በፓኪስታን ደግሞ የሄሮይን ሱሰኞች ቁጥር በ 1979 ከነበረበት ምንም ወይም ዜሮ መጠን በ 1980 ወደ 5,000 ሊያድግ በቃ። ከአራት አመት በኋላ ደግሞ ሳይታሰብ 1.3 ሚሊዮን ደረሰ። ይህም በተባበሩት መንግስታት አጠራር “በተለየ ሁኔታ አስደንጋጭ”የሚል ስያሜን አጎናፀፈው።

በ 1986 የወጣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሪፖርትም ኦፒየምን “ትንሽ ገንዘብ የሚጠይቅ፣ ቶሎ የሚያድግ እና በቀላሉ ተጓጉዞ የሚሸጥ በመሆኑ በጦርነት ለደቀቀች ሀገር ተስማሚ ተክል ነው።” ሲል ገልፆታል።

ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ የአፍጋኒስታን አየር ለተክሉ በጣም የተመቸ እንደሆነ በሪፖርቱ ተያይዞ ተገልጿል። በሲአይኤና በሶቪየት ተወካዮች መሀከል የተደረገው ጦርነት እረፍት አልባ ሰቆቃን በሚያስከትልበት ወቅትም የአፍጋን ገበሬዎች በተስፋ መቁረጥ ስሜት ትልቅ ትርፍ ወደሚያስገኘው ኦፒየም እርሻ ስራ ገቡ። የገበሬዎቹ ሀሳብም ትልቅ ጭማሪ እያሳየ የነበረውን የምግብ ምርት ዋጋ ለመቋቋም የተዘየደ ነበር።

በተመሳሳይ መልኩ የሀገሪቱ ተዋጊ ሀይላት በተቆጣጠሯቸው ቦታዎች ላይ የሚገኘውን ህዝብ የመሰረታዊ ምግብ አቅርቦት ለማድረስ ሲሉ የአደንዛዥ እፁን ማምረትና መነገድ ጀመሩ። በ 1980ዎቹ የሙጅሀዲን ተዋጊዎች ከሩሲያ መንጠቅ የቻሏቸውን በአፍጋኒስታን የሚገኙ ነፃ ቀጠናዎችን ለማስተዳደርም ኦፒየምን መጠቀም ጀመሩ።

በዚህ መሰረትም ከአደንዛዥ ዕፁ አምራች ገበሬዎች የሚገኘውን ትልቅ ገንዘብም በግብር መልክ ቀረጥ በማስከፈል ስራውን አቀለለ። በጊዜው የሲአይኤን የጦር መሳሪያ ለማድረስ ወደ አካባቢው የሚሄዱ አጋጓዦችም በመልሱ ወደፓኪስታን የኦፒየም ዕፅ ይዘው እንደሚመለሱ ኒውዮርክ ታይም በተለያየ ጊዜ ፅፏል።

ቻርለስ ኮጋን የተሰኙት የሲአይኤ የቀድሞ ሀላፊም በ 1995 በግልፅ የአፍጋኒስታን ዘመቻውን በተመለከተ እውነታውን ይፋ አደረጉ። ሰውየው በእማኝነታቸው “የእኛ ዘመቻ በቻልነው አቅም ሁሉ በቀድሞዋ ሶቪየት ላይ ጉዳት ማድረስ ነበር። በወቅቱ የነበረውን የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ለመመርመርም ጊዜውም አቅሙም አልነበረንም።

“ለዚህ ነገር ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልገናል ብዬ አላስብም። ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ ውድቀት ተከስቷል። አዎ! ነገርግን ዋነኛው ኢላማ እቅዱን መቷል። ሶቭየቶች አፍጋንን ለቀው ወጥተዋል።” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በረጅም የጊዜ ሂደትም የአሜሪካ ጣልቃገብነት በአካባቢው ላይ የማይሻር ጠባሳ ፈጥሮ መፍትሄ ለመስጠት በሚከብድ መልኩ ተጠናቋል። አሁንም ግን በአፍጋኒስታን ያለው ሁኔታ መረጋጋት የጠፋው ነው፡፡ በታሊባን እና በአፍጋን መንግስት መሀከል የሚደረገው የእርስበርስ ጦርነትም እንደቀጠለ ነው፡፡

ነገርግን ለዚህ የተረበሸ አካባቢ እና ለከሰረው የውጭ ፖሊሲ በተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች የተጠቆሙ የመፍትሄ አማራጮች አሉ። ይህም በዋነኛነት በሀገሪቱ ላይ ከፈሰሰው የተትረፈረፈ ያልተገባ የወታደራዊ ወጪ ጥቂቱን ለግብርና ማዋል ቢቻል በኦፒየም ምርት ላይ የተመሰረተ ኑሮ ያላቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎችን ነፃ ማውጣት እንደሚቻል የሚገልፅ ነው።

ያኔ ድር ያደራባቸው እርሻዎች ዳግም እንደሚያብቡ፤ ድራሻቸው የጠፉ የከብት መንጋዎች ዳግም እንደሚታዩ እና በመጨረሻም የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ እገዛ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከአድቃቂው ጦርነት በፊት የነበረው የመስኖ ልማት እርሻ በአፍጋኒስታን ገጠሮች እንደሚያንሰራራ ይታመናል፡፡

ይህ መሳካት ከቻለም አፍጋኒስታን የአለም ቀዳሚዋ የአደንዛዥ ዕፅ መናኻሪያና የዕፁ ገፈት ቀማሽ መሆኗ ቀርቶ በየአመቱ የተደጋገመባት የነውጥ አባዜ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊገታ ይችላል፡፡

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.