የሳማሪታን የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው

0
766

የሳማሪታን የቀዶ ህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ በቀዶ ህክምና ስፔሻላይዝ ያደረገ የመጀመሪያው ልዩ ማዕከል ይሆናል፡፡ የሳማሪታን የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ቅዳሜ ታህሳስ 7፤ 2010 ዓ.ም የሚከፈት ሲሆን የተለየና የወቅቱን የቀዶ ህክምና ቴክኖሎጂ፣ የቅድመና ድህረ ቀዶ ህክምና ክፍሎች፣ የምርመራ ክፍል ያሉትና ስመ-ጥር የሆኑ የቀዶ ህክምና ባለሞያዎችን የያዘ ነው፡፡ አዲሱ የህክምና ማዕከል ለህሙማን ዘላቂ የላቀ የቀዶ ህክምና አገልግሎትን የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት የቀዶ ህክምና አገልግሎት ከማይሰጠው የአሜሪካን የህክምና ማዕከል ጋር ትስስር አለው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪው የሆነ የቀዶ ህክምና ስፔሻልቲ ማዕከል የተመሰረተው በአራት ግለሰቦች ማለትም ዶ/ር አከዛ ጠአመ፣ ሜላት አባተ፣ አፈወርቅ አስገዶም እንዲሁም ፍሬወይኒ ዓለም በ148 ሚሊዮን የኢት. ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ማዕከሉ ሲከፈት በሁለቱ ተቋማት አማካይነት ምቹና ልዩ አገልግሎቶችን ለህሙማን በሰፊው እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡

 

የማዕከሉ የጋራ መስራች የሆኑት ዶ/ር አከዛ ጠአመ ማዕከሉን ለመክፈት ያነሳሳቸውን ምክንያት አስመልክቶ ሲገልፁ “ባለቤቴ ሜላት እና እኔ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ውይይቶችን ከህሙማንና ቤተሰቦቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ አድርገናል፡፡ ይህም በርካታ ወላጆች ዘመናዊ መሳሪያዎችና ብቁ ባለሙያዎች የያዘ የህክምና ማዕከል እጥረት በመኖሩ ይህን ለማግኘት ያላቸውን ብርቱ ፍላጎት በጥልቀት ለመገንዘብ ችለናል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ የልብ-ለልብ የውይይት ጊዜ ለአገልግሎት የሚሆን ተመጣጣኝ ክፍያ ለመክፈል ፍላጎቱ እንዳላቸው ተረድተናል፡፡ ወዲያውኑም ወደ ውሳኔ በመግባት በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች እስኪዳረስ ድረስ የተሻለና ዓለም-ዓቀፍ ደረጃን የጠበቀ የቀዶ ህክምና መስጫ ማዕከል ለመገንባት ቁርጠኛ አቋም ያዝን” ይላሉ፡፡

እንደ አርትሮስኮፒክ አጠቃላይ የዲስክ (የዳሌ) ንቅለ ተከላ (አርቴፊሻል ዲስክ መተካት) እና አርትሮስኮፒክ የጉልበት ላይ ቀዶ ህክምና ያሉ በውጭ ሃኪሞች በዘመቻ መልክ በየጊዜው ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ከዚህ ማዕከል መከፈት ጀምሮ በሳማሪታን ልዩ የቀዶ ህክምና መስጫ ማዕከል የሚሰጡ ይሆናል፡፡ ማዕከሉ ከዚህም በተጨማሪ ዘመናዊ የምርመራ አገልግሎት ሶፍትዌር እና ሲቲ ስካን ማሽን፣ የተማከለ የኦክስጅን መስጫ ክፍል እና ለተሻለ ህክምና ወደ ሌላ ተቋም ይላኩ የነበሩ ከፍተኛ ክትትል የሚያስፈልጋቸው ህሙማንን ባሉበት ለማከም የሚያስችል ባለ 8 አልጋ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡

በማዕከሉ ከሚሰጡ የላቁ የህክምና አገልግሎቶች መካከል “የህይወት አድን አካውንት” የተሰኘ አገልግሎት ይጠቀሳል፡፡ ዶ/ር አከዛ ስለአገልግሎቱ ሲናገሩ ፤ “ማንኛውም ግለሰብ በትንሹ የ50.000 የኢት. ብር በስሙ ማስቀመጥ ይችላል፡፡ አስቸኳይ ህክምና በሚያስፈልግበት ጊዜ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ከዚህ ተቀማጭ በመጠቀም ለአስቀማጩ ፣ ለእሱ/እሷ ቤተሰብ አባል ወይም አስቀማጩ ለፈቀደለት ሌላ ሰው ፊርማ ባዘለ ቀላል ደብዳቤ (በማዕከሉ የሚዘጋጅ) ወይም የአባሉን ስም፣ የሂሳብ ቁጥሩን እና ተቀማጩን የገንዘብ መጠን በመጥቀስ በሚላክ የኤስኤምኤስ መልዕክት አልግሎት የሚያስገኝ ነው፡፡ አስቀማጮች በዚህ አገልግሎት መርካት ባልቻሉ ጊዜ ተቀማጩን የአባልነት መዋጮ በማንኛውም ጊዜ መልሶ መውሰድ ይችላሉ፡፡ እናም በዚህ መርሃ-ግብር በመሳተፍ የሚያጎድሉት ምንም ነገር እንደሌለ በቀላሉ ለማየት ይቻላል” ብለዋል፡፡

የሳማሪታን የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከበርካታ መንግስታዊና ህዝባዊ ተቋማት ጋር ግንኙነት የመሰረተ በመሆኑ የማዕከሉን መልካም ተሞክሮዎች በሌሎች ለመተግበር እና ለማገዝ ያስችለዋል፡፡

የማዕከሉ የድንገተኛ አደጋ እና የልዩ ክትትል ክፍሎች ከማዕከሉ በተረፈ በበለጠ የሚደራጁ እና በአሜሪካ የህክምና ቦርድ እንዲሁም የድንገተኛ ህክምና ስፔሻሊስቶች የሚገመገሙ ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውጭ የሚገኙ ሃኪሞች በማዕከሉ መገኘት ሳያስፈልጋቸው በቴሌሜድስን አገልግሎት አማካይነት በማዕከሉ የሚገኙ ህሙማንን ለመከታተል ያስችላቸዋል፡፡

የሳማሪታን የቀዶ ህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ በቀዶ ህክምና ስፔሻላይዝ ያደረገ የመጀመሪያው ልዩ ማዕከል ሲሆን የወቅቱን የቀዶ ህክምና ቴክኖሎጂ፣ የቅድመና ድህረ ቀዶ ህክምና ክፍሎች፣ የምርመራ ክፍል ያሉትና ስመ-ጥር የሆኑ የቀዶ ህክምና ባለሞያዎችን የያዘና ለህሙማን ዘላቂ የላቀ የቀዶ ህክምና አገልግሎትን የሚሰጥ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.