የታላቁ ሩጫ አጭር ዳሰሳ

0
659

በትናንናው ቀን ”100 million reasons to work together for girls”  በሚል መፈክር በተካሄደው ታላቅ የሩጫ ፌስቲቫል ላይ ከ44 ሺ ሰዎች በላይ የተገኙበት ሲሆን ብዙ አዝናኝ፤ አስቂኝ፤ እንዲሁም አሳዛኝ ክስተቶች የተካሄዱበት ነበር፡፡

Great Ethiopian Run 2017

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጲያ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ ኦክቶበር 2000 ዓ.ም በሀይሌ ገብረስላሴ፤ ፒተር ሚድልብሮክ እና በአቢ ማስፊልድ የተጀመረ ሲሆን የመጀመሪያው ውድድር 10000 ሰዎች እና ከዚያ በላይ የተሳተፉበት ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ውድድር ስኬታማ አትሌቶችንም ያወዳደረ ሲሆን ቀነኒሳ በቀለ፤ ስለሺ ስህን፤ ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም፤ ወርቅ ነሽ ኪዳኔ እንዲሁም ጥሩነሽ ዲባባ ከፍተኛውን ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቀው ነበር፡፡ ይህ ዝግጅት ብዙ ታዳጊ አትሌቶችን ያፈራ ሲሆን የተለያዩ ጎብኝዎችን የሚያሳትፍ ነው፡፡ ታላቁ ሩጫ ውድድር ብዙ ዓመታዊ መፈክሮችን ያዘለ ሲሆን በዘንድሮው ደግሞ ለሴቶች መነቃቃትን እንዲፈጥር ተደርጎ የተዘጋጀ ነበር፡፡

በዚህ ታላቅ ዝግጅት ላይ የተለያዩ የንግድ ስራዎች በግላቸው ለተሳታፊዎች አገልግሎት ሲሰጡ ነበር፡፡ በስም የሚታወቁ ሬስቶራንቶች በተንቀሳቃሽ መልክ ፒዛ፤ በርገር፤ ሳንዱዊች፤ ጁስ እንዲሁም የተለያዩ ምግቦች እና መጠጦች ሲሸጡ ነበር፡፡ እንዲሁም ተሳታፊዎች በረዶ፤ ውሀ፤ ሳንቡሳ፤ ጣፋጭ ዳቦ እንዲሁም የመሳሰሉትን ከግል አዟሪዎች ላይ ሲገዙ ነበር፡፡ በቦታውም ከሩጫ ዝግጅቱ ባሻገር የተለያዩ የንግድ መዳረሻዎች የታዩበት ነበር፡፡

ይህ ዝግጅት የውጪ ሀገር ዜጎች፤ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም  የተለያዩ ታዋቂ የአለማችን ተፅእኖ ፈጣሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አይነስውሩ ዴቭ ሄሊ ይገኝበታል፡፡ ዴቭ ሄሊ በ2008 ዓ.ም በተካሄደው 7ቱ ማራቶን ውድድር በመወዳደር የመጀመሪያው አይነስውሩ ሯጭ ሲሆን ለተለያዩ አካል ጉዳተኞች ተፅዕኖ ፈጣሪና አስተማሪ ነው፡፡ ዴቭ ሄሊ በትዊተር ገፁ ‹በጣም የሚመስጥ የኢትዮጲያ ውድድር› በማለት የተለያዩ ፎቶዎችን ተነስቶ አስፍሯል፡፡

በውድድሩ ላይ ሁለት ተሳታፊዎች ራሳቸውን ስተው ከወደቁ በኋላ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም ነገር ግን ህይወታቸውን ማትረፍ አለመቻሉን የውድድሩ አዘጋጆች በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ ዘግበዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች አስቂኝ እና አዝናኝ ክስተቶች የተካሄዱ ሲሆን ተሳታፊዎች በውድድር ቲሸርቶቻቸው ጀርባ የሚለጥፉት ጥቅሶችና ፅሁፎች አነጋገሪና ዘና የሚያደርጉ ነበሩ፡፡

በዚህ ውድድር በወንዶች ሰለሞን በረጋ ከደቡብ ክልል 28፡36፡01 ሰዓት በመግባት አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ሞገስ ቱማይ ከመሶቦ 28፡38፡09 ሰዓት በመግባት እና  የግል ተወዳሪው ዳዊት ፍቃዱ 28፡51፡01 ሰዓት በመግባት ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

ከሴቶች ደግሞ ዘይነባ ይመር የኢትዮጲያ ንግድ ባንክን በመወከል 32፡30፡06 ሰዓት ላይ 1ኛ በመውጣት ግርማዊት ገብረግዜር ከትግራይ ክልል በ 32፡32፡06 ሁለተኛ ሆና አጠናቃል ፎተን ተስፋይም በ 32፡38፡09 ከሞሰቦ ሶስተኛ በመውጣት ውድድሩን ማጠናቀቋል አዘጋጆቹ አሳውቀዋል፡፡

አዲስ ኢንሳይት በዚህ ውድድር ላይ ህይወታቸውን ላጡ ተሳታፊዎች ጥልቅ ሀዘን ይሰማዋል፡፡ ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለጓደኞቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.