የአማራና የኦሮሞ የትሥሥር መድረክ የፈጠረው ኪሣራ

0
540

በፈቃዱ ዓለሙ

ትናንት በባህርዳር ከተማ የአማራና የኦሮሞ የጋራ መግባባት ጉባኤ በሰላም ተጠናቋል፡፡ መቼም ትናንት እንደኔ የታዘበ ካለ ሴረኞችና ጥቅመኞች አንደበታቸው ታሥሮ ከሁለቱ ባለመድረኮች በላይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንድነት ዝማሬ በየሰዓቱ በማኅበራዊ ገጾች የብሥራት ዜና ሲለጠፍና ነጋሪት ሲጎሰም መዋሉ አገራዊ ደስታ እንጅ ሌላ ምን ትሉታላችሁ?

“የውሸት ክምር በአንድ ድንጋይ (እውነት) ይናዳል” እንዲሉ ለለፉት 26 ዓመታት ሁለቱን ህዝቦች ሲያጣሉ የኖሩ የፖለቲካ ወለድ ኩሸት ፈጠራዎች ሁለቱን ህዝቦች ሲያናቁሩ ኖረዋል፡፡ ይሄ ኩሸት በትናንቱ መድረክ በሁለቱ ህዝቦች አንድነት ጉባኤ ላይ ጧፍ በመለኮስ በሬ ወለድ የፖለቲካ ጥቅመኞች የተፈጠሯቸውን የውሸት ታሪኮች የጥናት ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ብርሀኑ ለሜሶ ከቅርብ አመታት ወዲህ የተፈጠሩ የታሪክ ትንታኔዎች ትክክል አለመሆናቸውንና ከትርፉ ይልቅ ኪሣራ ማምጣታቸውን በጥናታቸው አመላክተዋል። በሁለቱ ሕዝቦች መድረክ ላይ ፕሮፌሰር ፈቀሬ ቶሎሳ የተገኝቶ ቢሆን ምኞቴን አሳበቀው፡፡

አለቃ አፅሜ የኦሮሞ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው፣ “በውኑ መምህራኑ ትልልቅ አለቆችም እጨጌዎችም ነገሥታቱም ሳይፈሩ ጽሕፈት ተምረው የዘመናቸውንና የወራቸወነን ታሪክ ጽፈውልን ቢሆን ለእኛ እንዴት ያለ ክብር ኑረዋል፤ ዳሩ በማይቻል ነገር ይጋደሉ ነበር፡፡” እንዳሉት ጥናት አቅራቢው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው “የኦሮሞ የአማራ 19ኛው እና 20 ኛው ክፍለ ዘመን በትክክል አለመፃፉ በታሪክ ላይ የፈጠረው ክፍተት የአማራው ገዥ መደብ እና የአማራውን ህዝብ አንድ ማድረግ፣ እንደጨቋኝ መቁጠር የህዝቡን መስተጋብር መሰረት ያላደረገ የልሂቃን ፖለቲካም የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ሸርሽሮት ቆይቷል በማለት ያለፈውን መሰረት አድርጎ የብሄር ጭቆና አለ ብሎ ማሰብ የሁለቱን ብሄሮች አንድነት አሳስቷል” ብለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲከኞች የሚገለጿውን ”ጠባብ” እና ”ትምክህተኛ” የሚሉ ያልተገቡ የፖለቲካ ቃላትን ማጥፋት እንደሚገባ አሳስበዋል። ታዲያ የታሪክ ሽንቁር የሆነው የአኖሌ ሃውልት መቆም የልብ ደስታ የሰጣቸው ፖለቲከኞች ዛሬ ይሄን ሲሰሙ የት የገቡ ይሆን? በየመድረኩ የስንቱን ኢትዮጵያዊ ልብ የሠበሩ የጅምላ ስድብና የትውልድን ትሥሥር የሚንዱ ”ጠባብ”ና “ትምክህት” የዘወትር ልጠፋቸው ምን ይውጠው ይሆን? መንግሥትና ፓርቲ ልዩነት የሌለለ እስኪመስል ድረስ ሁሉም አሠራርና አወቃቀር በፓርቲያዊ አስተሳሰብ ተተብትበው ስንቱን አቂያቃሩት?

መድረኩ ፖለቲካውን ቀይሮታል

“ኦሮሞ መገለጫው አብሮነት እና አንድነት ነው፡፡ ሞጋሳ እና ጉድፊቻ ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ አማራውም አንድነት ወዳጅ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ተመሳሳይ ሥነ-ልቡና አላቸው፡፡ እናም የሁለቱ አንድነት ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ልዮ ምእራፍ ይከፍታል” ለእኔ ለሁለቱ ህዝቦች ብቻ ሳሆን አገሪቱን ለሚመሩት ፖለቲከኞችም እስከ ዛሬ የመጡበትን መንገድ ትተው አገሪቱን ተጨማሪ የመምራት ፍላጎት ካላቸው አማራጭ መንገዱ ወዴት እንደሆነ ፍንትው አድርጎ አሳይቷቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ሰሚ ካለ፡፡ ሌላው የሁለቱ ሕዝቦች ትሥሥር በዚህ ከቀጠለ ደግሞ የሀገሪቱን ፖለቲካ መቀየሩ አይቀርም፡፡የክልሎቹ እርምጃ በዚህ ከቀጠለ የሀገሪቱ ፖሊቲካ ለውጡ የኢትዮጵያ ታሪክ መልሶ ከፍ እንደሚል ጥርጥር የለውም፡፡ የሁለቱ ታላላቅ ብሔሮች ትሥሥር በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነታችን ይበልጥ እያጎለበተ ኢትዮጵያዊነትን ያወዳጃል፡፡

 

የብሔረሰብ ፖለቲካ ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት የፈጠራ ታሪክ  ህዝብን ከህዝብ እያጋጨ ብዙ ደርዝ የነኩ ክፋቶች “በባለእዳዎች” ላይ ሲፈጸሙ ኖረዋል፡፡ አንዱ ረጋጭ ሌላው ተራጋጭ እየተደረገ ከጥላቻ ሐውልት በላይ በየመድረኩ “ጠባቦች” “ትምክህተኞች” እየተባለ ፖለቲካ ሲዘወር ኖሯል፡፡ የትላንቱ መድረክ ግን የፖለቲካ መዘወሪያ የሆኑትን ቃላት ጥፋትን እንጅ ሰላምን እንዳልሰበኩ በተጨባጭ አሳይተዋል፡፡ በጥናታቸው ማጠቃለያም ምሑራንና ፖለቲከኞች የአንድነት ሚናን መጫወትና የፖለቲካ ምሕዳሩን በዚህ ደረጃ ሊያሰፉት እንደሚገባ አሳስበዋል። ከላይ ከከፍተኛ ተቋም ጀምሮ እስከ ታች ባለው መዋቅር በየመድረኩ የተለየ አሳብ የሚያራምዱ ግለሰቦች ሳይቀር እንዲህ ዓይነት አሳቦች የ“አጠባቦች” ናቸው፣ እንዲህ ዓይነት አመለካከቶች የ“ትምክህተኞች” ናቸው እየተባሉ በጅምላ እውነት መስለው ዘልቀው ነበር፡፡ ከእንግዲህ ግን ከህዝብ በላይ የሚሆን ፖለቲካ ያለ አይመስለኝም፡፡ “የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ትሥሥርና በኢትዮጵያ ግንባታ ያላቸው ሚና” በሚል ጥናታቸውን ያቀረቡት የታሪክ ምሑሩ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ብርሀኑ ለሜሶ፣ “የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሣ የኦሮሞው ታሪክ የመገንጠል ሆኖ በውሸት ተቀርጿል፡፡ ኦሮሞ መገለጫው አብሮነት እና አንድነት ነው፡፡ ሞጋሳ እና ጉድፊቻ ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ አማራውም አንድነት ወዳጅ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ተመሳሳይ ሥነ-ልቡና አላቸው፡፡ እናም የሁለቱ አንድነት ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ልዮ ምእራፍ ይከፍታል” ብለዋል፡፡ በብሔረሰብ ፖለቲካ ተንሸዋሮ ነጻ ሙህራዊ የመድረክ ውይይቶች እየከሰሙ በመምጣታቸው ምክንያት የትናንቱ መድረክ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ንግግርና የሁለቱ ጥናት አቅራቢዎች አሳብ እንደ ተአምር በየማኅበራዊ ገጾች የደስታ ሲቃ ሲለጠፉ የዋሉት ለዚህ ነው፡፡

የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት ኢትዮጵያዊነት “ስስ” ነው ያሉት፣ አማራውና ኦሮሞው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ በየአቅጣጫው በባህል፣ በወግና በአኗኗር እንዲሁም በጋብቻ ተዋልዶና ተዛምዶ  ስለሚኖር ነው፡፡ ከፖቲከኞች እና ከጥቅመኞች ይልቅ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በችግሩ ውስጥ ሆኖ እንኳን ነገሩን ፉርሽ ለማድረግ አልፎ አልፎ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በአንድነቱ ላይ መረባረቦችን የሚያሳየው ለዚህ ነው፡፡ የኦሮሞ አባ ገዳዎቸ እንዳሉት “በኦሮሚያ ክልል አንድ አማራ ወንድ እና ኦሮሞ ሴት ተጋቡ፡፡ ወንድየው ኦሮምኛ አይችልም፡፡ ሴቷም አማርኛ አትችልም፡፡ ግን በመንፈስ ተግባቡ እና ተጋቡ፡፡ ተጋብተው የሁለቱንም ቋንቋ ተመማሩ፡፡ እንኳንስ በቋንቋ በመንፈስ ይግባባሉ፡፡ ይሄ የሆነው ዛሬ አይደለም፡፡ ከ50 ዓመት በፊት ነው፡፡ እና አማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች እንዲህ ናቸው፡፡ በመካከላችን ማንም አይገባም፡፡ አማራ እና ኦሮሞ ሐይቅ ነው፡፡ በሐይቁ ውስጥ ያሉ ነገሮች ሊረብሹን አይገባም፡፡ አንድ ነን፡፡” ይሄ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት የተከናወነው ኹነት በአማራውና በኦሮሞው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና አስተዋይነት ዘር፣ ፖለቲካ ሳይለይ ሲከናወን የቆየ ትልቅ እሴታችን ነው፡፡ እንግዲህ መድረኩ የብሔረሰብ ፖለቲካ አራማጆች ካሉበት አፍዝዝ አደንዝዝ ነቃ እንዲሉ እድሉን ያመቻቸ ይመስለኛል፡፡

 

የትሥሥር መድረኩ ቀጣይነት

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ወደ ሥልጣን ከመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቃላት ባለፈ የተግባር ሥራቸውን በዚህ የጋራ መግባባት መድረክ አንድ ብለው በመጀመራቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ “ይሄ ህዝብ ምንም ብትሉ አንድ ነው” እንዳሉት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድርም አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ወንድሞቻቸውን ተቀብለው በማስተናገድ በመድረኩ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ሲሰብኩ በመዋላቸው እንዲሁ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ባይጋባም እንኳ መቀሌ ተወልዶ ሻሸመኔ ባደገበት ሀገር፣ ጎንደር ላይ ተወልዶ ከንባታ ባደገበት ሀገር፣ አምቦ ላይ ተወልዶ ጎጃም ባደገበት ሀገር፣ ጉራጌው፣ ደርዜው፣ ወላይታው፣ ሀድያው፣ ከንባታው፣ ሶማሌው፣ ኮንሶው፣ ሐመሩና ቤንሻጉሉን ሁሉም የትም የሚኖርባት ሀገር ውስጥ መድረኩ ለሁሉም ልዩ ትርጉም አለው፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና እና የሚጋጩ ህልሞች” በሚለው መጽሐፋቸው፡፡ “በእኔ እምነት ሁለቱም ከታሠሩበት የታሪክ እሥር ቤት ወጥተው በጋራ የዲሞክራቲክ አጀንዳ ላይ ተስማምተው በመሀል መንገድ ላይ ካልተገናኙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአሁኑ ትውልድ ዘመን ፈቀቅ የሚል አይመስለኝም፡፡” ያሉት  አሁን እውን መሆን ጀምሯል፡፡ ነገር ግን የሁለቱም ክልሎች ርእሰ መስተዳድሮች ከዚህ በበለጠ ከቃላት ባለፈ የተግባር ሥራዎች ይጠብቋቸዋል፡፡ ይሄ ህዝብ በቃላት ሲደለል የኖረ ህዝብ ስለሆነ የመድረኩ ፈንጠዝያ የጠላት ልብን እንዳቆሰለ ሁሉ በተግባር ሥራዎች ደግሞ የበለጠ ሲዋደድና ለአገር ኹለንተና እጅ በእጅ ሲረባበረብ ማሳየት ይገባል፡፡ ፖለቲካዊ ትርፍን ብቻ ዓላማ አድርገው በየጊዜወው ሢነሡ የነበሩ አስተሳሰቦች፣ ግጭቶች እንዲሁም የታሪክ ክፍተቶች ተጠንተው መማማሪያ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያችንም ከፍ ትላለች፡፡ ጥናት አቅራቢዎቹ እንዳሉትም የሁለቱን አንድነት መልሶ ለመጠገን በመሠረተ ልማት ማገናኘት፣ ቋሚ የባህል ልውውጥ ማድረግና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠንከር፣ የሁለቱም የጋራ ታሪካቸውን ማጥናት፣ የቋንቋ ትምህርት በሁለቱም ክልሎች ቢካሄድ የተባሉትን ማስኬድ አዋጭ ነው፡፡

 

በማጠቃለያየ የተከበሩ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ንግግር ያለምንም ጭማሪ ይሄው ብያለሁ፡፡ “……ኢትዮጵያዊነት የራሱና የጋራው በሆኑ ባህሎች፣ ወጎች፣ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ትውፊቶችና ጠንካራ የአብሮነት እሴቶች ጥምረት ድርና ማግ ሆኖ የተሠራ የከበረ ማንነት ነው፡፡ ይህ ለዘመናት በአንድ የተገመደ አብሮነት እና ውህደት ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት በንፋስ ተወዛውዞ የሚወድቅ ወይም የሚሰበር ሳይሆን ይበልጥ ሥር እየሰደደ፣ እየጠበቀና እየጠለቀ የሚሄድ ታላቅ ሃይል ያለው ማንነት ነው፡፡ ታሪኩን ጠብቀውና አዳብረው ያቆዩን አባቶቻችንም ቢሆኑ ምንም አይነት የማንነት ልዩነት ሳይገድባቸውና ሳያደናቅፋቸው የሁላችን የሆነችውን ውብ ኢትዮጵያን በደምና ባጥንታቸው መስዋእትነት ጭምር አጥር ሆነው ከጠላት ወረራ በመጠበቅ ከልዩነት ይልቅ አብሮ የመቆም፣ አብሮ የማሸነፍ፣ አብሮ የመድመቅ፣ አብሮ የማደግና የመለወጥ ታሪኩንም ሁሉ ጠቅለው ለሁላችንም አስረክበውናል፡፡

እኛ የዛሬዎቹ ባለተራዎች በዚህ መንገድና ደረጃ የተረከብናትን ሀገር የአንድ ወገን ወይም የአንድ አካባቢ ሃብት ብቻ አድርገን የምናያት ሳይሆን የሁላችንም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ መኖሪያችን መሆኗን ተገንዝበን፣ ይበልጥ አንፀንና በሁለንተናዊው የእድገት መስክ ሥምሪት ገንብተንና አበልፅገን ልዩነታችን ውበታችንና የአንድነታችን መሰረት ሆኖ እንዲያገለግል ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና ኖሮት ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ታላቅ አደራ ያለብን ትውልዶች ነን፡፡ ኢትዮጵያዊነት የህብረት፣ የአብሮነት፣ የአንድነትና የመከባበር ምልክት መሆኑን ያልተገነዘቡ የሩቅና የቅርብ ጠላቶቻችን ዛሬ ዛሬ የራሳችንን ድክመቶች መፈናጠጫ እርካብ እያደረጉ ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ፈልፍለው እየገቡ፣ ውሸቱንም ጭምር እየደራረቱ ሊለያዩን ሲፋትሩ ይታያል፡፡ ይህ ድርጊት የኢትዮጵያዊነት ማንነት በወጉ ጠንቅቆ ካለመረዳት የሚነሳ ከንቱ ድካም መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጎዝጉዞ ተቀባይነት፣ አንጥፎ አሳዳሪነት፣ ፈትፍቶ አጉራሽነት፣ ተቀብሎ፣ አጥቦና ስሞ ሸኚነት በጥቅሉ ወንድማማችነት ሲሆን አስገራሚና ውሁዳዊ የሚያደርገው ደግሞ ይህን መሰሉ አኩሪ እሴት የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል መሆኑ ነው…….”

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.