የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን እጣ ፈንታ

0
558

በፈቃዱ ዓለሙ

ኢትዮጵያ ካለፉት ጊዚያት ይልቅ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ብዙ ፖለቲካው፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መደነቃቀፎች ታይተውባታል፡፡ ከሁሉም በላይ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በየጊዜው እየቆዩ ብቅ የሚሉት እነዚህ መጎረባበጦች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ የችግሩ ክፋት ማህበራዊውን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውንም ከጎዳው ቆይቷል፡፡ በየጊዜው ለሚከሰቱት መጎረባበጦች ልዩ ልዩ ምክንያቶች ቢለጠፍባቸውም ችግሩ ግን በየጸደዩ እብጠቱን ማፈንዳት አላቆመም፡፡

ምንም እንኳን ችግሩ የእከሌ ብቻ ነው ባይባልም ዳንኤል ክብረት (ዲ/ን) እንዳለው ችግሩን ለመፍታት እስከዛሬ የተሄደበት መንገድ ተመሳሳይ በመሆኑ ውጥረቱን ማዳከም አልተቻለም፡፡  ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ርእዮት ሳይሆን ጥንት በነበረው ባህላዊና መንፈሳዊ ትሥሥር ነው አንድነታቸውን ማጠናከር የሚወዱት፡፡ ጎጣዊ በሆነ ፖለቲካ መቼም ሰላማቸውን አያገኙም፡፡ ለዚህም ነው ከፖቲከኞች እና ከጥቅመኞች ይልቅ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በችግሩ ውስጥ ሆኖ እንኳን ነገሩን ፉርሽ ለማድረግ አልፎ አልፎ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በአንድነቱ ላይ መረባረቦችን የሚያሳየው፡፡

ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሱ መፍትሄ እንዲያገኝ ከመሥራት ይልቅ አንዳንዱ በማጣፋት፤ አንዳንዱ በማራገብ ሌላው ፖለቲካውን እና ኢኮኖሚውን መከታ በማድረግ በዝምታ እያለፉ ሙያዊና ማኅበራዊ ግዴታቸውን ወይም ሓላፊነታቸውን ስለማይወጡት መገናኛ ብዙኀን ጥቂት ማለት መልካም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከደረሰባት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መደቋቆስ አንጻር ያለፈውን እና መጻዩን የመገናኛ ብዙኀን እጣ ፈንታም ከወዲሁ መጠቆም አስፈላጊ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን 1997 . ወዲህ

የቁጥር አፈ ቀላጤው መንግሥት ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ጀምሮ በማኅበረሰብ ሬዲዮ፣ በኅትመት እና በብሮድካስት ዘርፍ በቁጥር ደረጃ መስፋፋት እንዳለ የብሮድካስት ባለሥልጣን ከሁለት ዓመት በፊት ለኢዜአ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን መገናኛ ብዙኀኑ በፖለቲካው፣ በማህበራዊውና በኢኮኖሚው እድገት ላይ ምን ያኽል  አስተዋጽኦ አበርክተዋል የሚለው ጥያቄ መልስ አያገኝም፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የቀድሞው አሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በንግግራቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ብዙ መሻሻሎች እንደሚቀሩት እና የክህሎትና የሥነ ምግባር ክፍተቶች እንዳሉበት ጠቁመው ማለፋቸው ይታውሳል፡፡ የሚገርመው ችግሩ አለመቀረፉን በማመላከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ሳምንት ፓርላማ ላይ ይሄን ንግግር ደግመው አንሥተውታል፡፡ ይሁን እንጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ቢሉም ከ1997 ዓ.ም ወዲህ አሣሪ በሆኑ ልዩ ልዩ ሕጎች እና በመንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደነቃቀፉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባልዳበረ ሙያዊ ክህሎት እና ደካማ በሆነ እይታ ወይም ገዥው መደብ ምን አለ ከማለት ውጭ የአብዛኛው ህብረተሰብ ድምፅ የማይሰማባቸው የተንሸዋረረ ዘገባቸው ሄዶ ሄዶ ጠንካራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብርክ ብርክ ሲላቸው ታይቷል፡፡

ጥናቶች እንደ ሚያመለክቱት ከ1997 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት በ1987 ዓ.ም ካሳየው አሳብን በነጻነት የመግለጽ (እያንዳንዱን ዜጋ ጨምሮ ሁሉንም መገናኛ ብዙኀን ማለት ነው) መብት ጋር ፍጹም ተቃራኒ ሆነ መጥቷል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው (ጠንካራውም ደካማውም) የኅትመት ሚዲያዎች በአንድም በሌላም መንገድ ከገቢያ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ብዙ ጋዜጠኞች ተሰደዋል፣ ልዩ ልዩ አሳቦች ድምፅ አልባ ሆነዋል፣ የመንግሥት ሚዲያዎችን ጨምሮ የቀሩት ጥቂት የኅትመት ሚዲያዎችም መንግሥትን እለት እለት ከማወደስ ውጭ በተጨባጭ መንግሥትን ሲተቹ አልታዩም፡፡

የቁጥጥሩ ውጤት ማንን ጎዳ?

የቁጥጥሩ ውጤት ማንን ጎዳ የሚለው ጥያቄ ካልተመለሰ መንግሥትም መገናኛ ብዙኀንም በሀገሪቱ መጻይ እጣ ፈንታ ላይ ችግር መፍጠራቸው አይቀርም፡፡ በተለይ መንግሥት ያለፉትን  አሥራ ሁለት እና አሥራ ሦስት ዓመታት ወደ ኋላ ሔዶ ካልፈተሸ፤ መገናኛ ብዙኀንም አዘጋገባቸውን እና ሙያዊ ክህሎታቸውን ካላሻሻሉ ወይም ከዘልማድ አሠራራቸው ካልወጡ ፖለቲካውንም ህዝቡንም ከማደናገር አልፈው ሀገራዊ አንድነቱ ላይ አደጋ መቀሠራቸውን አያቆሙም፡፡

መንግሥት በመገናኛ ብዙኀኑ ላይ ያሳየው ጥብቅ ቁጥጥር ውጤቱ ገና አያደገ ላለው ዲሞክራሲያችን እንቅፋት ከመሆን አልፎ በዜጎች ላይ ጉዳት አምጥቷል፡፡ መንግሥትን ብቻ ሲያንቆለጳጵሱ የኖሩት መገናኛ ብዙኀን የተለየ አሳብ ያላቸውን ዜጎች ድምፅ የሚያስተናግድ በመጥፋቱ ችግሩ ሁሉ ተንከባሎ ተንከባሎ እንደሰሞኑ ዓይነት ወረርሽኝ ሲመጣ መገናኛ ብዙኀኑ ድንብርብራቸው ሲወጣ ታይቷል፡፡ በዲሚክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ልዩ ልዩ አሳቦችን ካላስተናገዱ፣ ዜጎች አሳባቸውን በነጻነት ካልተነፈሱ መገናኛ ብዙኀን ለዲሞክራሲ መስፈን የሚደርጉት እንቅስቃሴ ደካማ ይሆናል፡፡  በሌላ በኩል ባልዳበረ የሙያ ክህሎት እና የሥነ ምግባር ችግር ውስጥ አፈ-መንግሥት እና መሀል ሠፋሪ የሆኑት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ከመንግሥት ጋር የመሠረቱት ልቅ የሆነ ዝምድና ውጤቱ ሄዶ ሄዶ “አንቺው ታመጭው አንቺው ታሮጭው” ሆኖባቸዋል፡፡

ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚወነጨፉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን መንግሥት ሁሉንም ነገር ወደ ፍርድ ቤት እንዲወስድ አስገድዶታል፡፡ ምክንያቱም እንደ ሀገር መንግሥትም ሆነ ሌላው አካል ሲሳሳት እረፉ የሚል መገናኛ ብዙኀን ስላልነበረ፤ ምክንያቱም ዜጎች በቂ መረጃ ይዘው በልዩ ልዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መድረክ በማመቻቸት በኩል ሓላፊነት የወሰደ የሚዲያ ተቋም ስላልነበረ፤ ምክንያቱም በተለይ የመንግሥት ሚዲያዎች ከህዝብ ግንኘኙነት ተለይተው ስለማይታዩ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ሕጎች ሲወጡ ህዝቡ እንዲወያይና እንዲተች መገናኛ ብዙኀኑ ሓላፊነታቸውን ስላልተወጡ የሚሉት አሳቦች ውኃ ያነሣሉ፡፡

መንግሥት በመገናኛ ብዙኀን ላይ ያሳየው ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር “ባሏን ጎዳሁ ብላ…..” እንዲሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ እንኳን ዜጎችን ሲያማርሩ የነበሩ ብልሹ አሠራሮች፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች፣ የከፍተኛ ሹማምንቶች ልቅ የሆነ ሙስና (የሀገር ዝርፊያ ቢባል ይሻላል አንዳንዶቹ ዝርፊያቸው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው አይመስልምና)፣ እና ሌሎች ሀገራዊ ችግሮችን የሚሰማ፣ የሚያሰማ በመጥፋቱ ለብጥብጥና ለዜጎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች መንግሥት መገናኛ ብዘኀኑን ተቆጣጠርኹ ብሎ ፖለቲካውንም ህዝቡንም እንዲጎዳ አድርጎታል፡፡ ጥብቅ የሆነው የመንግሥት ቁጥጥር ሄዶ ሄዶ ብሮድካስት ባለስልጣኑን የሚመራው የመንግሥት ካድሬ፣ ብቸኛ የዜና ምንጭ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን፣ የየሚዲያዎቹ ቦርድ ሰብሳቢዎች የመንግሥት ሹማምንቶች፣ ብቻ በሁሉም በኩል መንግሥት የሌለበት የለም፡፡ ይሄ የሚያሳየው ነጻና ሚዛናዊ መረጃ ወደ ህብረተሰቡ እንዳይደርስ የራሱ ተጸእኖ እንዳለው ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከ1997 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ የግልም ሆነ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ወገንተኝነት እና መሳሳብ (የግሉ ሚዲያ ተቃዋሚዎችን በመደገፍ እና የመንግሥት ሚዲያዎች ደግሞ ገዥውን መንግሥት በመስበክ) (one-sided and polarized) መሆናቸውን ልዩ ልዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ የግል ሚዲያዎች (ምን አልባት ከሬዲዮ ዘርፍ ከአንድ ጣቢያ ባልዘለለ) በብሮድካስቱም ሆነ በኅትመት ዘርፍ ፖለቲካውን ተጣብቀው ኢኮኖሚውን እንጅ ህብረተሰቡን ማእከል ያደረገ አቋም ያላቸው የሉም፡፡ በቃለ መጠይቅ ከታጨቁ ዝግጅቶች ውጭ ቁምነገርኞች ናቸው ብለን ልንጠራ የምንችለው አንድ ወይም ሁለት ይሆናሉ፡፡ በሳምንት ከአንድ እና ከሁለት በላይ የአየር ሰዓት ከጣቢያዎቹ ወስደው በአጋርት የሚሠሩትም በባህር ማዶ ባህል የተለከፉ በመሆናቸው ትውልዱ የኔነት/ሀገራዊ ስሜት እንዳይኖረው የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በቅርብ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚለው ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በሥራ ተቋማቸው ውስጥ በራስ መተማመን እንደሌላቸው እና ከቅድመ-ምርመራ ወደ ዝምታ  (from self-censorship to silent) እንዳመሩ ያትታል፡፡ (ሙላቱ ፣2017፣ ገጽ 18) ይሄ የሚያሳየው መንግሥት በመገናኛ ብዙኀን ላይ ያለው ቁጥጥር ምን ያክል ጠኔ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ቁጥጥሩ ከተቋም አልፎ በጋዜጠኞች ላይ ክፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩን ጥናቱ በዝርዝር ያትታል፡፡

ሰለዚህ ባለፉት አሥራ ሁለት ዓመታት ጥብቅ የሆነው የመንግሥት ቁጥጥር በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ጉዞ ላይ አሜካላ የበዛበት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ እናም “ሀገራዊ እብደቱ” በእነዚህ እና መሰል ጉዳዮች ከተጸናወተን ቆይቷል፡፡ ልክ እንደ ማኅበራዊ ሚዲያ (Social Media) የባህላዊው ሚዲያ (ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን፤ Traditional Media) መረጃዎችን በማዛባት ከሀገራዊ አንድነት ይልቅ ጸባጫሪነትና ገቢያ ተኮር የሆኑ አካሄዶች በሀገሪቱ የሚዲያ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ በአጠቃላይ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በኅትመትም ሆነ በብሮድካስት ዘርፍ መገናኛ ብዙሃን የየመንግሥታቱ የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ከመሆን ባለፈ የብዙሃን አሳቦችን ማስተናገድ ላይ ተሰኗቸው ዐይተናል፡፡

የመገናኛ ብዙሃኑ ቀጣይ እጣ ፈንታ  

አሁን ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን የሥራ ኹኔታ ከላይ በተዘረዘሩት ልዩ ልዩ ምክንያቶች ተቋማቱን ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞችን ጭምር የራስ መተማመናቸውን እና ሥነ-ልቡናቸውን ሠርቆታል፡፡ የሚዲያ ተቋማቱም ሆኑ ጋዜጠኞች በተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥሮች እንደሰሞኑ ዓይነት ሀገራዊ አንድነት ላይ በዘገባዎቻቸው ሲልፈሰፈሱ ታይታዋል፡፡ አንዳንዱ ፖለቲካዊ ጥቅሙን ፈልጎ ከሚዲያነት ይልቅ ፖለቲካዊ ድርጅት ይመስል አንዱን ከአንዱ ጋር ለማቃቂያር ተፉጨርጭሯል፡፡ አንዳንዱ ኢኮኖሚያዊ ልብሱን አጣፍቶ መሀል ሲሰፍር፣ ሌላው ደግሞ ሙያዊ ግዴታውንና ማኅበራዊ ሓላፊነቱን ወደ ኋላ ገሸሽ አድርጎ  በዝምታ አልፏል፡፡ ምን አልባት በቅርቡ ጥሩ መሻሻሎችን እያሳዩ ለመጡት ATV እና OBN የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አይዟችሁ በርቱ ማለት ግን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት መገናኛ ብዙኀን ወደፊት የህዝብ ሚዲያ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነውና፡፡ እናም የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙኀን ቀጠይ እጣ ፈንታ እንዲህ ነው ለማለት የሚከተሉት አሳቦች ትኩርትን ይሻሉ፡፡ አለበለዚያ የመጣው ሁሉ “ላግባሽ” ማለቱን አያቆምም ወይም ደግሞ ከፖለቲከኞች ይልቅ ለመገናኛ ብዙኀን ወላፈኑ ይከብዳቸዋል፡፡

  • ያም ሆነ ይሄ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን እውነታ ለመንግሥትም ለህዝቡም እንደማይበጁ የተለያዩ ቀያይ መብራቶችን እያሳዩ ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ያልፋል ወይም መንግሥት አልፎ መንግሥት ይተካልና መገናኛ ብዙኀን የአንድ ወገን ዝምድናቸውን ትተው ሁልጊዜም ከህዝብ ወገን መሆን እንዳለባቸው ማስገንዘብ መልካም ነው፡፡ በየትኛውም አስቸጋሪና አጣብቂኝ ኹኔታ፤ በየትኛውም ሀገራዊ ጉዳይ መገናኛ ብዙኀን ወገንተኝነታቸው ለህዝብ መሆኑን መረዳት ሙያዊ ግዴታቸው ነው፡፡ አለበለዚያ እደግመዋለሁ “የመጣው ሁሉ ባሌ ነሽ” ማለቱ ነገም አይቀርም፣
  • መገናኛ ብዙኀኑ ህዝቡ ችግሬ ነው በሚላቸው ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ህዝቡን ሲደቁሰው፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር በህዝቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚው ኑሮ ላይ ጫና ሲያሳድር እና ፍርድ ሲጓደልበት የህዝቡን ድምፅ መገናኛ ብዙኀን ማሰማት አለባቸው፡፡
  • ከሙያዊ እና ከማኅበራዊ ሓላፊነት አንጻር መገናኛ ብዙኀን ከህዝብ ይልቅ የአንድን ፖለቲካ ርእዮት ዓለም ለማስፈጸም ትኩረት ያደረጉ የኤድቶሪያል ሕጎቻቸውን/ፖሊሲዎቻቸውን መፈተሸ መጀመር አለባቸው፣
  • ህዝቡ በቂ መረጃ አግኝቶ በልዩ ልዩ ፖሊሲዎች፣ ሕጎች እንዲሁም በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ተሣታፊ እንዲሆን ቀድሞ የነበውን የመረጃ ክፍተት አትብቆ መሙላትና መሥራት፣
  • የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ሀገር ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችንና ሌሎች ታላለቅ ሀገራዊ ብልሹ አሠራሮችን ሚዛናዊ ሆነው መዘገብ ላይ ከፍተኛ እጥረት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ስለሆነም የሚዲያ ተቋማቱ በተለይም ጋዜጠኞች ራሳቸውን በልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ለማሻሻል መዘጋጀት አባቸው፡፡ ምንም እንኳን አንድ ጥናት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች 80% ያኽሉ የተማሩ ናቸው ቢልም ቅሉ፣ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይና ትልልቅ አጀንዳዎችን የማወያየትና በህዝቡ ዘንድ የማስረጽ ችግር እንዳለ በልዩ ልዩ ጊዚያት የተፈጠሩ ኹነቶች ማሳያ ናቸው፡፡ (Skjerdal, 2017)

በአጠቃላይ ሁሉም አካል የድርሻውን ካልተወጣ ችግሩ ተዛዝሎ ጤነኛውንም በሽተኛውንም መልከፉ አይቀርም፡፡ እንደ አንድ ሀገር ጋዜጠኛ ግን ልዩ ልዩ ሙያዊ ሥልጠናዎችን እየወሰዱ እና ልምድን እያዳበሩ ጠንካራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውይይት እንዲያደርግ አጥብቆ መሥራት በጣም ወሳኝ ነው፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.