የሆሄ የስነ ፁሁፍ ሽልማት በትናንትናው እለት በብሄራዊ ቲያትር ተካሄደ ።

0
747

ትናንት ማምሻውን በአንጋፋው ብሄራዊ ቲያትር የመጀመሪያው ሆሄ የስነ ፁሁፍ መፃህፍት ውድድር ባለውለተኞችን በመሸለምና በሶስት ዘርፍ መፃህፍትን በማወዳደር ሽልማት አድርጎል ። ስነ ስርአቱ ይጀመራል ተብሎ ከተባለበት ሰዓት 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ዘግይቶ ነው የጀመረው ፤በአዳራሹ የነበሩትም አንጋፋ፣ ታዋቂ ሰዎችና ታዳሚው በተለያየ መልኩ ቅሬታቸውን ሲገልፁ ተመልክተናል።

ዝግጅቱ መነሻውን በፌደራል ማርሽ አጃቢነት ሁለት ኢትዮጵያ መጠሪያቸው በሆነ ዜማዎች በማሰማት ነበር መክፈቻውን ያደረገው። የመጀመሪያው ዜማ ፤ የአለም ፀሀይ ወዳጆ የግጥም ስራ እና የአበበ መለሰ ዜማ ድርሰት የሆነው በጥላሁን ገሰሰ የተቀነቀነው ኢትዮጵያ የሚለው ሙዚቃ ነበር። እሱን ተከትሎ ደግሞ ግጥሙና ዜማው የራሱ የሆነው በወቅቱ በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን የቴዎድሮስ ካሳሁን ኢትዮጵያ በመድረኩ በማሰማት ነበር የነበረውን ነገር ይበልጥ ያስቀጠለው።በአዳራሹም የነበረው ህዝብ የቴዲ ዜማ በማርሽ ባንዱ ሲሰማ የነበረው ስሜት የተለየ እንደነበር መመስክር ይቻላል።የተሰሙት ዜማዎች ከቀረቡ በኋላም በታዋቂው አርቲስት አለማየሁ ታደስ መድረኩን በመምራት ባለቅኔውን፣ ተርጓሚውንና ገጣሚውን ነብይ መኮንን በመጋበዝ ለየት ባለ መልኩ ነብይ ግጥሙን ከፌደራል ማርሽ ባንድ ጋር በመሆን የግጥም ስራውን ኣቀረበልን ።ከግጥሙ በማስታከክ ወደ መድረኩ የመጣው የሽልማት ስነ ስርኣቱ ሀላፊ የሆነው ኤፍሬም ብርሃኑ ስለ ሽልማት ስነ ስርዓት አስፈላጊነት በስነ ፅሁፍ የተሻለና ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበትና የመፅሕፍት ሽያጭ የተሻለ እና ገቢው የተመጣጠነ እንዲሆን በማሰብ እንዲሁም ዝግጅቱን ለማዘጋጀት አንድ አመት እንደፈጀ፤ በ2008 አመት የታተሙ መፃህፍትን እንዳወዳደሩና ከዛ ባሸገር የድምፅ ኣሰጣጡ 80 በመቶ በተመረጡ ዘጠኝ ዳኞች የተሰጠ ሲሆን 20 በመቶ ደግሞ በኣጭር የፅሁፍ መልክት በህዝብ እንደነበር በስፋት በመናገረ ነበር። በንግግሩ ማሳረጊያ ላይ አጠገቡ በመሆን ላገዙት ለሁሉም ምስጋናውን በማቅረብ ከመድረኩ ወርዷል።

በመጀመሪያ በምሽቱ ዝግጅት ባለውለታዎችን በመሸለም ነበር ጅምሩን ያደረገው። በሚዲያ በኩል ለስነፁሁፍ የላቀ ኣስተዋፅኦ በማበርከት ሸገር 102.1 ባለውለታ በመሆን ተሸልሟል።ሽልሟቱንም ከአአዩ የስነ ጥበባትና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳሬክተር ሰኣሊና ገጣሚ ኣገኝውኣደነ ድል ነሳው እጅ ተቋሙ ተቀብሏል። ሁለተኛው የባለውለታ ዘርፍ ደግሞ በረጅም ዘመን የትምህርት መስፋፋት የላቀ ባለውለታ ተብለው የተመሰገኑት ኣቶ ማሞ ከበደ ናቸው።አቶ ማሞ ከበደ በብሄራዊ የትምህርት ዘመቻ ወቅትም 17 ዙሮችን በዋና መኮንንነት በመምራት እንዲሁም ትምህርት በሬድዩ በማዘጋጀትና በማስተላለፍ ትልቅ ስራ የሰሩ ናቸው ።ሽልሟቱን ከአአዩ የዓለም ዓቀፍ ትምህርት ክፍል ዳሬክተር ደመቀ አንቺሶ እጅ ከተቀበሉ በኋላም እንደዚ በማለት ሀሳባቸውን ገልፀዋል።”እኔ ሸምግያለው ነገር ግን እኔ በሰራሁት ስራ ስሸለም ሌሎች ይህን አይተው ጥረት ያደርጋሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ተናግረዋል። ሶስተኛ ባለውለታ ተብሎ የተሸለመው ደግሞ እንደ ሸገር ኤፍ ኤም ይሄም ተቋም ነው።ለአይነስውራን መፅሕፍት ተደራሽ በማድረግ ባለውለታ በማለት በርካታ መፅሕፍት ለአይነ ስውራን ያዘጋጁትን አዲስ ህይወት የአይነስውራን ማህበር በማመስገን ሽልማቱን ከሴት ደራሲያን ማህበር መስራችና ደራሲ የዝና ወርቅ እጅ ማህበር ተቀብሏል።ማህበሩን በመወከልም ንግግር ያደረጉት እንስት እንዲህ ብለዋል።”እኛ በከፈትናት ትንሽ ላይብረሪ ነገር ግን ለብዙ ህዝብ አገልግሎት የሚሰጠውን ተመልክቶ ስለሸለመን ሆሄን እናመሰግናለን” ብለዋል። ኣራተኛ ባለውለታ በመባል የተሸለሙት ደግሞ በረጅም ዘመን በጋዜጠኝነት ለስነ ፁሁፍ አበርክርቶ በማድረግ ጋዜጠኛና ተራኪ የወርቃማ ድምፅ ባለቤት የሆነው ደጀኔ ጥላሁን በመሆን ተመርጧል ። በዝግጅቱም ላይ ባለመገኝቱ እንዲሁም ተወካይ ባለመኖሩ ሸልማቱን ከአንጋፋው ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ይልማ ሳይቀበል ቀርቷል። አምስተኛ ባለውለታ ነው የተባለ ዘርፍ በረጅም ዘመን የስነፁሁፍ ሀያሲነት በሚል ኣንጋፋው ሀያሲ ኣስፋው ዳምጤ ተብሏል። ሽልማታቸውንም በተወካያቸው በደራሲ ሀይለመለኮት መዋል በኩል ተቀብለዋል። ሀይለመለኮትም ከብሄራዊ ቤተመፅሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጄንሲ ተወካይ ከወይዘሮ እስከዳር አስፋው ከተቀበለ በኋላ በንግግራቸው “ኣስፋውን ወክዬ መናገር ቢከብድብም ስለዝሆን ጥንቸልን ኣስተያየት ትስጥ ማለት ነው” በማለት ፈገግታ በማስጫር ሽልማቱ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ሌላው በመጨረሻ የህይወት ዘመን የስነፁሁፍ የላቀ ባለውለታ ተብለው የተሸለሙት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ነበሩ። ሽልማታቸውን እንዲሁም በማስታወስና በመዘከር ጋዜጠኛ ብሩክ ያሬድ ከፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ እጅ ተረክቧል።በመድረኩም ብሩክ አለቃን በሚገባና በተሻለ መልኩ በማመስገን አክብሮት እንዲሰጥ ብሎ ከአለቃ ጋር አብሮ ይለፉ የነበሩት በመጥቀስ ንግግሩን በሚያስደንቅ መልኩ ኣቅርቦልናል።

በመቀጠል ዝግጅቱ ወደ ሁለተኛው ክፍል የሽልማት ስነ ስርዓት ያመራው በመካከሉ የውዝዋዜ ዝግጅት በማቅረብ ነበር ።ውዝዋዜውም በሀሁ የውዝዋዜ ቡድንና የብሄራዊ ቲያትሩ አንጋፋ ተወዛወዥ በሆነው ሰለሞን ተካ ጋር በመሆኑ ከንባብ እና ከመፃህፍት በማያያዝ ታዳሚውን አዝናንተዋል። ከውዝዋዜው መልስ በሶስት ዘርፎች ለ5 እና 6 ወራት ያወዳደሩትን የመፃህፍት ሽልማት ነበር የተደረገው። አዘጋጆቹ እንደተናገሩት በ2008 የወጡ 23 የረጅም ልብወለዶችን፣ 39 የግጥምና 12 የህፃናት መፃህፍትን አወዳድሮ በሁለቱ ማለትም በግጥምና በረጅም ልቦለድ ኣምስት እጩዎች እንዲሁም በህፃናት ደግሞ 3 እጩ በማስቀረት ነበር ለምሽቱ ስነ ስርዓት የቀረቡት። በህፃናት መፅሕፍት ዘርፍ ተሻላሚ መሆን የቻለው፤ ከነበሩት ሶስት እጩ መፅሕፍት ሁለቱ ወደመጨረሻ ዙር የደረሱለት አስረስ በቀለ በቤዛ ቡችላ አሸናፊ ሆናል ። አስረስም ሽልማቱን ከቋንቋና ስነፁሁፍ መምህር ረ/ፕ ደረጄ ገብሬ እጅ ከተቀበለ በኃላ “ይሄን ሽልማቴን በህይወት ኖረው አባባ ተስፋዬ በተመለከቱ” ሲል በቁጭት ተናግራል።

በግጥም ዘርፍ አሸናፊ መሆነ የቻለው ደግሞ በእርድና ፍርድ መፅሕፍ አበረ ኣያሌው ተመርጦ ከአያልነህ ሙላቱ እጅ ሽልማቱን ወስዷል።የተሰማውን ነገር እንዲገልፅ የተጠየቀው ኣበረም በመጀመሪያው መፅሀፉ በመሸለሙ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል። በረጅም ልብወለድ ዘርፍ አሸናፊ ደግሞ የአዳም ረታው የስንብት ቀለማት መሆን ችሏል። አዳም በዝግጅቱ ላይ ባለመገኝቱ ወንድሙ እሱን በመወከል ከአንጋፋው ደራሲ ሳህለስላሴ ብርሃነ ማርያም እጅ በመቀበል የሽልማት ስነ ሰርዓቱ አብቅቷል።

በመጨረሻም ድህረ ገፃችን በተለያየ ዘርፍ ባለውለታ እንዲሁም ተወዳድረው እውቅና የተሰጣቸውን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የሆሄ አዘጋጆችም ላደረጉት ነገር ክብር እየሰጠን የተሻለና ቀጣይነት እንዲኖረው በመመኝት እናጠቃልላለን።

በዳግም ታምሩ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.