የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዋች ቁጥር 8.5 ሚሊዮን ደረሰ

0
633

በ2009ዓ.ም በበለግ አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተደረገ የምግብ ዋስትና የዳሰሳ ጥናት ለቀጣይ አምስት ወራት 8.5 ሚሊዮን ህዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተገለፀ፡፡

የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በበለግ አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች የምግብ ዋስትና የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ይኸው ጥናት በሰብል አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከግንቦት 15 እስከ ሰኔ 15፣2009 ዓ.ም ድረስ ተካሂዷል፡፡

በጥናቱ የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ፣ የእርሻ ስራ እንቅስቃሴ፣ በማሳ ላይ ያለው የሰብል ሁኔታ፣ የምርት ግምት፣ የግጦሽ እና የውሀ አቅርቦት፣ የእንስሳት አቋም እና የምርት ሁኔታ፣ የሰው እና የእንስሳት ጤና እንዲሁም በወቅቱ እየተሰራጨ ያለው የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች የስርጭት ሁኔታ በመዳሰስ የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና ሁኔታ ለመገምገም የተቻለ ሲሆን በተገኘው ውጤት ቀደም ሲል 7.8 ሚሊዮን ከነበረው የተረጂ ቁጥር ወደ 8.5 ሚሊዮን ከፍ በማለት ለቀጣይ 5 ወራት ማለትም ከነሀሴ 2009 እስከ ታህሳስ 2010 ዓ.ም የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

ይኸው የዳሰሳ ጥናት ሰብል አብቃይና አርብቶ አደር በሆኑት አካባቢዎች የተከናወነ ሲሆን በዘንድሮ አመት የተረጂው ቁጥር የጨመረበት ምክንያቶች የበልግ ዝናብ መዛባት፣ የመኖና ግጦሽ ማነስ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎችም የምርት መቀነስ እና የውሀ እጥረት መሆናቸው በጥናቱ ላይ ተመላክቷል፡፡

በጥናቱ ላይ በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስተባባሪነት የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ሴክተር ቢሮዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ የሁለትዮሽ ስምምነት ያላቸውና ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሁኑ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

ከብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.