የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ከሌሎች ባንኮች የአውቶሜትድ ክፍያ ማሽኖች (ኤቲኤም) ገንዘብ ማውጣት የሚችሉበት አሰራር ለጊዜው እንዲቆም ተደረገ።

0
1623

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የኤቲኤም ካርድ አስመስሎ በመስራት በሌሎች ባንኮች ገንዘብ ለማውጣት ሙከራዎች እየተደረጉ በመሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ከሌሎች ባንኮች የአውቶሜትድ ክፍያ ማሽኖች (ኤቲኤም) ገንዘብ ማውጣት የሚችሉበት አሰራር ለጊዜው እንዲቆም ተደረገ።

የሌሎች ባንኮች ደንበኞች ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ ከሌሎች ባንኮች ኤ ቲ ኤም ማሽኖች ገንዘብ ማውጣት ይችላሉ ተብሏል።

ይህ የተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የበጀት አመቱን የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ነው።

የባንኩ የፋይናንስ ተቋማት ምክትል ገዥ አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የንግድ ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖቻቸውን በጋራ እንዲጠቀሙ የሚያስችለው አሰራር ለሀገሪቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግር የመታየት አዝማሚያ ተስተውሎበታል።

አሁን የተከሰተውን በሀሰተኛ ካርድ ገንዘብ የማውጣት ሙከራ በተመለከተ የኢት ስዊች ቦርድ እየመከረበት መሆኑንም ገልፀዋል።

በዚህም ሁሉም ባንኮች ተመሳሳይ የካርድ ስታንዳርድ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የየትኛውም የንግድ ባንክ ተጠቃሚዎች ደንበኛ ካልሆኑበት ባንክ የኤ ቲ ኤም ማሽን ገንዘብ ማውጣት የሚችሉበት ብሄራዊ የክፍያ ስርዓት ሚያዚያ 12 ቀን 2008 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል።

በ80 ሚሊየን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው ኢት ስዊች አክሰዮን ማህበር ስርአቱን ከመዝርጋት ጀምሮ ሂደቱን በበላይነት እየመራ እንደሚገኝ ይታወቃል።

በካሳዬ ወልዴ fanabc

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.