የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገር ባህሎች ክፍል ሁለት/ የማኅበራዊ ሥራ የደቦ ዘፈን

0
984

የሀገራችን ሰው ብዙውን ጊዜ ሥራን በኅብረት መሥራት ይወዳል፡፡ ይኸውም ደቦ ወይም ጅጌ እየተባለ ይጠራል፡፡ አንድ ሰው አንድ ስራ ለመስራት ብዙ ጊዜና ጉልበት ስለሚጠይቀው ከሌሎች ሰዎች ጋር በመተባበር ለምስራት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህም በአካባቢው ከሚገኙት ሰዎች ጋር ወንፈል በመግባት የግብርና ስራውን ያከናውናል፡፡ በቤትም ውስጥ ሴቶች ለጥጥ ስራ ጅጌ ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም ከሀገሩ ዕድር ወይም ደንብ የወጣ መስተንግዶ አይዘጋጅም ምክንያቱም ወይኖ አረሰው ወይኖ ጎረሰው እንደሚባለው እንዳይሆን ነው፡፡

በህብረት እርሻውን አርሰው ዘሩን ሲዘሩ በመከራ ወቅት ሰብሉን ሲሰበስቡና ሲወቁ ለማበረታታት ሲባል ከመሐከላቸው አንደኛው ልዩ ልዩ ግጥም ስልት ባለው ዜማ እያወረደ ሥራውን ያከናውናሉ፡፡ በሚጋበዙበትም ጊዜ በመዝናናት ደስታቸውን በሆታ ይገልጣሉ፡፡ ዘፈኖቹም እንደጊዜው ሁናቴ የግብርናን ስራ በየመልኩ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ የሚሰጡትን ትርጉም አስተውለን ስንመረምር የሰው ልጅ ግብርናን የተለየ  ሞያ አድርጎ መያዝ ያለበት መሆኑን በሬዎች ለገበሬዎች ታላቅ ረዳትና የስራ ጓደኞች መሆናቸውን ሰብል በሥራው አድካሚ ቢሆንም ለሰው ሕይወት ጠቃሚነቱን እህል ያለው ፈርዛዛ፤ ብር ያለው ቀበዝባዛ መሆኑን ሰነፎች ለምግብ ሲገኙ ለስራ መታጣታቸውን ፤… ይህንንና ይህን የመሳሰለውን ሁሉ እየዘረዘረ የሚያሞግስና የሚዘልፍ ነው፡፡ ከዚህም የምናገኘው ቁም ነገር የሰው እጅ ሳያዩ ፣ሳይራቡ፣ ሳይጠሙና ሳይታረዙ ለመኖር መሬትን አርሶ ራስን መቻል ይበልጣል የሚል ነው፡፡

ከግጥሞቹ ውስጥ በጥቂቱ

(የበሬውን ውለታ ስለመግለጥ)

እሽሩሩ በርዬ እሽሩሩ፤

አንተ በሠራኸው ይኖራል ሀገሩ፤

 

በሬና ገበሬ ቢጣሉም አይበጅ፤

እንዲያው ሰተት ብሎ ይጠመዷል እንጂ፡፡

 

በሬ የሌለው ሰው ማዕረግም አይደርሰው፤

ከሸንጎም ቢወጣ ሰው አይዋሰው፡፡

 

በሬ አንተን የጠላ ጎኔ አንተን የጠላ፤

የገና የጥምቀት ይለምናል ጠላ፡፡

 

ምነው በቅዳሜ ምነው በእሁድ ቢያርሱ፤

ከባለጸጋ ቤት ከሚመላለሱ፡፡

 

በርዬ በርታልኝ ትንፋሽህ ምንድነው፤

ምርቱ ለኔ ቢሆን ገለባው ለአንተ ነው፡፡

 

በርዬ ምሩቁ ምሩቁ፤

አንተ ካልዞርክበት አይሰበር ምርቁ፤

በዱላ ቢመቱ በመንሽ ቢደልቁ፤

 

የበሬን ውለታ መጫወት ነው ማታ፤

በሰፊ ገበታ በዋንጫ ጋጋታ፡፡

 

ከኢትዮጵያ የባህል ጥናት ባለን እንወቅበት በብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወ፤መ የተወሰደ

 

 

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.