ስነ-ሰብ/ሰዓሊ ለማ ጉያ

0
1627

ሻምበል ለማ ጉያ ምሥራቅ ሸዋ ውስጥ ከደብረ ዘይት ከተማ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ድሎ በምትባል መንደር ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ሻምበል ለማ ጉያ ከግብርና ሙያ ተነስተው ወደ ት/ቤት የገቡት በ17 አመት እድሜያቸው ነው፡፡ ለተወሰኑ አመታት በትምህርት ከቆዩ በኋላ በመምህርነት ሙያ ለመሰለፍ በመሻት ወደ መምህራን ማሰልጠኛ ት/ቤት ገቡ፡፡ በመምህራን ተቋሙ ብዙም ሳይቆዩ የበለጠ የስራ ፍላጎት ያሳዩበት ወደነበረው የውትድርና ሙያ ለመሰማራት ወደ አየር ሀይል  ሄደው ገቡ፡፡

በኢትዮጵያ አየር ሀይል ውስጥ ተቀጥረው ሥራቸውን የጀመሩት በ1943 ዓ.ም ነበር፡፡ ለ25 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በ1968ዓ.ም ጡረታ በመውጣት ቀደም ሲል ያዝ ለቀቅ ያደርጉት ወደነበረው የስዕል ሥራ ተሰማሩ፡፡ የሻምበል ለማ ጉያን ከሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸው ለየት የሚያደርጋቸው ወንድሞቻቸውና ልጆቻቸው እንደሣቸው በስዓል ሙያ መሰማራታቸው ነው፡፡ ወንድሞቻቸው ቱሉ ጉያ እና አሰፋ ጉያ፣ ልጆቻቸው ደረጀ ለማ ጉያ፣ ነፃነት ለማ ጉያ እና ሰላማዊት ለማ ጉያ የሻምበል ለማን ፈለግ በመከተል በሥዕል ሙያ በርካታ ስራዎችን አበርክተዋል፡፡ በተናጠልና በወልም በተለያዩ ስፍራዎች አውደ-ርዕይ በማዘጋጀት የተመልካቹን አድናቆት አትርፈዋል፡፡

ሻምበል ለማ ጉያ በግልና እንዲሁም ከወንድሞቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በመሆን በአገር ውስጥ በአድስ አበባ እና ደብረዘይት፣ ከኢትዮጵያ ውጪ ደግሞ በኤርትራ-አስመራ፣ በናይጄርያ-ሎጎስ እና በሴኔጋል-ዳካር ስፍር ቁጥር የሌላቸው አውደ-ርዕዮች አቅርበዋል፡፡ ደብረዘይት መግቢያ ላይ  የአፍሪቻ ሙዚየም በሚል ስያሜ የተገነባው ጋለሪ ዘወትር ክፍት በሆነው የእሳቸውና የቤተሰቦቻቸው ኤግዚቢሽን ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚመጡ ጎብኚዎችን ማስተናገድ ከጀመረ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡

ሻምበል ለማ ጉያ የሚስሏቸው ስዕሎች ተፈጥሮን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ እና የተመልካቹን ውስጣዊ ስሜት ፈንቅለው የሚያወጡ ለመሆናቸው የፅሁፍ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ተስለው አድናቆትን ካስገኙላቸው ሥራዎች መካከል “የሸክላ ገብያ” እና “የደንክል ልጃገረድ” የተባሉት ሥራዎቻቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሻምበል ለማ ጉያ ለተደናቂ የሥዕል ሥራዎቻቸው እስካሁን ድረስ በርካታ ሰርተፍኬቶችና ልዪ ልዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡

ከፋንታሁን እንግዳ ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ ከጥንት እስከ ዛሬ መፅሀፍ የተወሰደ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.