የመረጃ ጦርነት ( Information Warfare)

0
942
brain icon

ስልጣኔ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፤ የሰው ልጅ ለሚያራምደው አለማዊ እና መንፈሳዊ ፍልስፍና ቦታ መስጠት ሲጀምር ለተለያዩ ጥቅሞች ሲባል ፤ ተጠቃሚ አካላት ይህን የሰው ልጅ ስነ-ልቦናዊ አመለካከት ለመቀየር ብዙ ሰርተዋል እናም ተሳክቶላቸዋል። እኛ ሰዎች አስቡ የተባልነውን ነገር ብቻ እንድናስብ ተደርገን ነው የተፈጠርነው? አዎ ከሆነ መልስዎ ፤ በከፊል ልክ ነዎት። በተለይም በዚህ መረጃ እንደ ጅረት በሚፈስበት ዘመን ስለተፈለገው ግለሰብ ፣ ቡድን ፣ ሀገር፣ ፆታ ፣ ሀይማኖት ወዘተረፈ አስተሳሰብ መቀየር ይቻላል።

ከጥቂት አመት በፊት የኢቦላ ወረርሺኝ ተከስቶአል ሲባል ፤ ከ100 ሰው 99ኙ በሽታው አዲስ በሽታ እንጂ በህክምናው ከታወቀ ብዙ አስርት አመታት እንዳሳለፈ አያውቁም። ጋዜጣው ኢቦላ ፣ የቡና ወሬ ኢቦላ ፣ ፀሎት ስለ ኢቦላ ሳር ቅጠሉ ሁሉ ስለ ኢቦላ እያብሰለሰለ አፍሪካዊ የሆነ ማንኛውም ሰው ለተወሰኑ ወራት አለም አቀፋዊ መገለል ደርሶበት ነበር። ግን የፓሪሱ የቻርሊ ሄብዶ መፅሄት ዋና መ/ቤት በአሸባሪዎች ከተጠቃ በኃላ የኢቦላ ጉዳይ በአንድ ጊዜ ተረሳ። ለዚህ ሚዲያው የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። አፍሪካውያን በበሽታ ፤ አረቦች በሽብር እንድንታወቅ የሚፈልግ አካል አለ ማለት ነው?

አሁን አሁን የአለም ሀያላን መንግስታት አለምን እየዘወሩ ያሉበት የመረጃ ጦርነት(Information Warfare) የሰው ልጅን ስነ-ልቦናዊ አስተሳሰብ በቶሎ መቀየር እንደሚቻል ስለሚያውቁ አብዛኛውን ሽኩቻ የሚያካሄዱት መረጃ ላይ ነው። በቀድሞው የአሜሪካ አስተዳዳሪ ዲሞክራቶች እምነት ፤ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትነትን ያሸነፈው በሩሲያ መንግስት በሚደረገው የተወሳሰበ የመረጃ ጦርነት ብለው በፅኑ ያምናሉ። የውሸት መረጃ እና ዜና(Fake News) ለአብዛኛው ሰው ተደራሽ በሆነው ኢንተርኔት ላይ የሚለቀቀው የ3ኛውን ወገን አስተሳሰብ ለመቀየር ነው።

ከአለማቀፋዊ ክስተቶች ወደ ሀገር ቤት አልያም ወደ መንደር ደረጃ ወርደን ምን ያክል የመረጃ ማጣመም ስራ ለግል እና ድርጅታዊ ጥቅም እንደሚውል ለመገንዘብ የPublic Relations ድግሪ አይጠይቅም። ለምሳሌ :- ምንም ያክል መጥፎ እንደ አርዬስ የተወገዘ አምራች ብዙም ሳይርቅ የገፅታ ግንባታ አካሂዶ ፤ በጥሩ የሚዲያ ስራ እራሱን አሁንም ተወዳጅ ምርት እንደሆነ አቅርቦ ፣ ስሙን ያጠፉት ሌሎች ተፎካካሪ አካሎች እንደሆኑ አክሎበት ለ1ሳምንት የሚሆን ማስተዋወቂያ ቢያስለፍፍ ሳናስብበው ሀፉ እንለዋለን። የፖለቲካው ትኩሳት ከባድ ስለሆነ ትግበራው ፖለቲካው ላይ ይክፋ እንጂ ለእያንዳንዱ አስተሳሰብ ሌላ ትይዩ(Parallel) አስተሳሰቦችን መፍጠር ይቻላል።

የመረጃ ፍሰት እና ተደራሽነት የበለጠ እየፈጠነ እና እየረቀቀ በሄደ ቁጥር ፤ እኛም በፍጥነት የመሸወዳችን እና ከሀሳብ ወደ ሀሳብ ፤ ከአመለካከት ወደ አመለካከት የመዝለላችን ፍጥነት ከፍ ይላል። አለማችን ላይ እርጋታ የማይታይበት ትልቁ ሚስጥር ይህ ሳይሆን አይቀርም። ኢንተርኔት እና የኬብል ቴሌቭዥን ባይኖሩ የሰው ልጅ የሚጎዳውን ያክል ተጠቃሚ ይሆናል። ቢያንስ ከሀሳብ ወደ ሀሳብ አይቅበዘበዝም። ዛሬ እስራኤልን ሲደግፍ የነበረ ከሳምንት በኃላ ፍልስጤምን ይደግፋል። ከ2 ሳምንት በኃላ ሁለቱንም እርግፍ አድርጎ ትቶ አሜሪካንን ብቻ ይደግፋል እያለ አዙሪቱ ይቀጥላል። የኢንተርኔት እና የኬብል ዜናዎች እንደ ጋዜጣ እትመት በሳምንት ሁለቴ እንኳን አዳዲስ ነገር ይዘው ቢመጡ የመሸወድ እና Manipulate የመደረጋችንን ጊዜ በቀናት አራዘምን ማለት ነው። የአለም ሰላም ከመረጃ ጋር ይገናኝ ይሆን እንዴ? ብዙ ተፈላሰፍኩ መሰለኝ። መልካም ቀን።

በ አማኑኤል ዘውዴ አሮን

 

 

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.