የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቫዮሊን ተጫዋች በሻህ ተክለማርያም (የሙዚቃ አቀናባሪ)

0
1091

አቶ በሻህ ተክለማርያም ከአባታቸው ከግራዝማች ተክለማርያም አጥናፉ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ የሺወርቅ ወለደደፃዲቅ በመጋቢት ወር 1912 ዓ.ም  በባሌ ክፍለ ሀገር በጎባ ከተማ ተወለዱ፡፡ ገና በለጋ እድሜ እያሉ አዲስ አበባ ውስጥ ስድስት ኪሎ አካባቢ  በሚገኘው በቅዱስ ማርቆስ ቤ/ክ ገብተው የአማርኛ ትምህርትና ፅህፈት መማር ጀመሩ፡፡ እስከ ስምንት አመታቸው ድረስ በአማርኛ የቀለም ትምህርት ከቆዩ በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ እና በኋላም በተፈሪ መኮንን ት/ቤቶች የፈረንሳይኛ ትምህርት ቀጠሉ፡፡ በዚያን ዘመን ነርሲስ ኬ ናልባንዲያን የሚባሉ አርመናዊ ሰው በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤ የዘመናዊ ሙዚቃ መሳርያ አጨዋወት ትምህርት ይሰጡ ስለነበር በሻህ ተክለማርያም ከተማሪዎቻቸው አንዱ ለመሆን በቁ፡፡ በመሀሉ ግን ሆለታ በሚገኘው የጦር ት/ቤ ተመልምለው ለእጩ መኮንንነት ስልጠና ገቡ፡፡ በውትድርና ሰልጥነው አንድ አመት ከቆዩ በኋላ ከሞግዚታቸው ጋር ባለመስማማታቸው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው መጡ፡፡

በሻህ አዲስ አበባ እንደመጡ ብዙም ሳይቆዩ ጣልያን መላ አገራችንን ወረረች፡፡በሻህም እንደማንኛውም ኢተዮጵያዊ ዜጋ ተሰደዋል፣ ተገርፈዋል፣ በመጨረሻም ታስረዋል፡፡ ከእስር ከተፈቱና አገርም ከተረጋጋ በኋላ ቫዮሊን የተባለውን የሙዚቃ መሳሪያ የመጫወት ችሎታ እንዳላቸው ታውቆ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በኩል ሸክላ እንዲያስቀርፁ ይጠየቃሉ፡፡  በጥያቄው ተስማምተው ቤተማርያም ዘወልዴ የተባሉ ሰው እያዜሙ እሳቸው በቫዮሊን እያጀቡ ተጫውተው ይቀረፃሉ፡፡ ሁኔታው የበሻህን ስሜት በማነሳሳት ለበለጠ ስራ አዘጋጀ፡፡ በመሀሉ ግን በት/ሚነስቴር ይቀጠራሉ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ በጊዜው የገንዘብ ሚኒስቴር በነበሩት አቶ አቶ መኮንን ሀብተወልድ ጠያቂነት ስራቸውን ለቀው የባህል ኦኬስትራ መሰረቱ፡፡ በዚህ ኦኬስትራ አማካኝነት የሰርግ ሥነ-ሥርዓትን የሚያደምቁትን ጨምሮ ብዙ የባህል ሙዚቃዎችን አቀናበሩ፡፡

በ1953 ዓ.ም በነሐሴ ወር ከልዩ ልዩ ክፍሎች ተወጣጥቶ ወደ ቻይናና ሶቪየት ህብረት የሄደውን የሀገር ባህል ሙዚቃ ባንድ በመምራት ከተጓዙት አንዱ ናቸው፡፡

1958 ዓ.ም ጀምሮ በዋናው ኤዲተር የአንድ ክፍል ሀላፊ ሆነው ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ 1967 ዓ›ም ጡረታ ወጡ፡፡ በሻህ በአደረባቸው ህመም 1987 ዓ.ም አርፈው በቀጨኔ መድኃኔአለም ቤተ ክርስትያን ተቀበሩ፡፡

 

ከፋንታሁን እንግዳ ታሪካዊ መዝገበ-ሰብ ከጥንት እስከዛሬ መፅሀፍ የተወሰደ፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.