የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገር ባህሎች ክፍል አንድ፤ ቀረርቱ ወይም ሽለላ

0
1082

ኢትዮጵያን አባቶች የጀብዱ ስራ በናላቸው እንዲቀረጽ ልጆቻቸውን ቀረርቱ እያሰሙ ያሳድጓቸዋል፡፡ ቀረርቱ ወይም ሽለላ ማለት የጦርነት ዘፈን ነው፡፡ ወይም ወታደር በጌታው ፊት በሰልፍ መካከልና በጨዋታ ላይ የወንዶችን ወኔ ለማነቃቃት በዜማ የሚያሰማው ቃል ነው፡፡

አቅራሪዎች በሰልፍ ውስጥ ወይም በግብር ላይ ጀግኖችን ልቡና በሽለላ እንደበገና አውታር እያቃኙ በየጦሩ ሜዳ የወደቁትን ለሀገራቸው ታላላቅ ጀብዱዎችን ሰርተው የሞቱትን የጦር ስልት በሆነ ዜማ በአማረ ድምፅ ምስጢር ያላቸውን ግጥሞችን ባሰሙ ጊዜ ባለሱሪዎችን በልጓም እንደተያዙ ፈረሶች ያቅበጠብጧቸዋል፤ ደማቸው እንዲፈላ አድርገው መቀመጥ እስኪሳናቸው ቦታ እስኪጠባቸው ያሟሙቋቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አላስችል ያላቸውና ባለወኔዎች ብድግ ብለው መፎከር ልማዳቸው ነው፤ ቀረርቱና  ፉከራ አይለያዩም ቀረርቱ ይቀድማል ፉከራ ወይም ድንፋታ ይከተላል፡፡

ከቀረርቶዎች ውስጥ አንዳንዶቹን የሚሰጡትን ስሜት ለማወቅ ይቻል ዘንድ ከዚህ በታች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

 

ንዳው ላሙን ናዳው ላሙን አቧራው ይነሳ

ይመጣ የለም ወይ ኮርማው እያገሳ፡፡

 

ካባቴ ባድማ ፍግ አታፍሱበት

ነዲዱ ቢጠፋ ረመጡ አለበት፡፡

 

እነዚያ ወረዱ እንውረድባቸው

አንበሳም አይደሉ እንደኛው ሰው ናቸው፡፡

 

በዛ ምጡ በዛ ምጡ ወይ እኛ አልወረድን

ወይ እነሱ አላመጡ፡፡

 

ጦር አይመጣም ሲሉት ይመጣል ድንገት

ደህና ደህና ጎበዝ መርጠው ካልቆዩት፡፡

 

በለው በለው ሲል ነው የጋሜ ኩራቱ

ሲትም ትዋጋለች ከረጋ መሬቱ፡፡

 

ሂድ ሲሉት ካልሄደ ና ሲሉት ካልመጣ

ስደደው ጎበዙን እጁን ይዞት ይምጣ፡፡

 

ሱሪህን ከፍ አድርግ ጎራዴህን ቀና

ከዚያም ቤት ከዚም ባለደም ነህና፡፡

እባክሽ እናቴ ውለጅልኝ መንታ

ቀኝ እጄን ስመክት ግራ እጄ ተመታ፡፡

 

ተው በለው ተው በለው ይሞታል

ሎጋው ሲወረወር አገዳ መስሎታል፡፡

 

ፈረሱንም ጋልበው ላቡ እስኪንቆረቆር

ነፍጡንም ተኩሰው ቃታው እስኪሰበር

ጦሩንም ወርውረው ሶማያው ይሰንጠር

አዳራሽ ሲገቡ አነገት ከማቀርቀር፡፡

 

አባት ጀግና ሆኖ ልጅ የፈራ እንደሆን

እናቱን ጠይቋት ዘር ለውጣ እንደሆን፡፡

 

በሚቀጥለው ክፍል ፉከራ ወይም ድንፋታን ይዘን እንመጣለን፤ መልካም ሳምንት፡፡

 

ከኢትዮጵያ የባህል ጥናት ባለን እንወቅበት በብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወ፤መ የተወሰደ፡፡

 

 

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.