ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰጠ የሃዘን መግለጫ

0
1292

በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ   ትላንት መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት  ላይ በተፈጠረ የቆሻሻ ክምር  የመደርመስ አደጋ እስከ ቅርብ ሰዓት ድረስ የ46 ወገኖቻችን ህይወት አልፏል፡፡ በተጨማሪም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ወገኖቻችን በአለርት ሆስፒታል ተኝተው ህክምና በመከታተል ላይ ሲሆኑ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው 20 የሚሆኑ ህክምና ወስደው ከሆስፒታሉ ወጥተዋል፡፡

 

አደጋው መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና የጸጥታ ሠራተኞች በሥፍራው በመገኘት የነፍስ አድን ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በህይወት የተረፉ ሰዎችን የማፈላለጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።

 

ከአደጋው የተረፉትን እና ህክምና አግኝተው ከሆስፒታል የወጡትን ወገኖቻችንን በጊዜያዊ መጠለያ አሰባስቦ የመርዳት እንቅስቃሴም ጎን ለጎን በመካሄድ ላይ ይገኛል።

 

ተጨማሪ የአደጋው ሰለባዎች ካሉ በነፍስ የማፈላለጉ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ከአደጋው ለተረፉት ወገኖቻችንንም አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያገኙ ይደረጋል። በዚህ አጋጣሚ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው በዚህ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎቻችን የኢፌዴሪ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ይመኛል።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

መጋቢት 3 ቀን 2009 ዓ.ም

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.