የአድዋው ዘመቻ

0
969
picture by: Abinet Teshome http://instagram.com/ab_onthestreet

 

የኢጣልያ  ጦር እጅግ ዘልቆ ወደ ትግራይ መግባቱ የሰሙት አጤ ምንሊክ ጦራቸውን ለማንቀሳቀስ ወሰኑ:: በዚህም መሰረት የክረምቱ ዝናብ እናዳቆመ መስከረም 7 ባስነገሩት አዋጅ በሚቀጥለው ወር ወደ ሰሜን እንደሚያቀኑ አስውቀው ማንኛውም ጉልበት ያለው የሸዋ ሰው ጥቅምት ወር ሳያልቅ ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን  ምሥራቅ 200 ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘውና ወረይሉ ከተባለችው ሥፍራ ደርሶ እንዲከት አዘዙ:: ከጎጃም ደምቢያ ቆራና በጌምድር የሚንቀሳቀሱት ወታደሮች ጨጨሆ ከተባለው ሥፍራ እንዲሰበሰቡ እንዲሁም ከሰሜን ወልቃይትና ጠገዴ በሚዘምቱት ወታደሮች ደግሞ መቀሌ እንዲሰባሰቡ ታዘዘ:: የራስ መኮንን ጦር ከሐረር ተጉዞ በጥቅምት መጀመሪያ ሳምንት ከዋናው ጦር ጋር ተቀላቀለ::

የአድዋ ዘመቻ ሲጀመርና ሠራዊቱ ከአዲስ አበባ ሲነሣ ከተማይቱ ገና የአስር አመት ብቻ ዕድሜ ነበራት:: የአጤ ምንሊክ ቤተመንግስት ከአንድ አመት በፊት ሲገነባና ጥቂት መኳንንትና ባዕዳን ነጋዴዎች በድንጋይ ቤቶች ቢያሳንፁም አዲስ አባባ አሁንም በአብዛኛው የድንኳኖች ከተማ ነበረች:: ገና በቅርቡ የተተከሉት የመጀመሪያዎቹ የባህር ዛፎችም ቢሆኑም አላደጉም ነበር:: አዲስ አበባ በአጠቃላይም ዛፍ አልባ መንደር ነበረች:: የከተማይቱ ሁለት ማዕከሎችም “አራዳ” የተባለው የገበያ ሥፍራና የንጉሱ ቤተ መንግሥት ነበሩ::

የአድዋ ጦርነት

ዘመቻው ሲጀመር የኢጣልያ ጦር በስተሰሜን የኢትዮጵያ ጦር ደግሞ በስተደቡብ ተሰልፈው የነበረ ቢሆንም የአድዋ ጦርነት ራሱ ሊደረግ ሲል ግን ሥፍራቸውን ለዋውጠው ጣልያኖቹ በምሥራቅ ኢትዮጵያውያኑ ደግሞ በምዕራብ ይገኙ ነበር ..

በሶስት ብርጌዶች የተከፈለው ዋነኛው የኢጣልያ ጦር አሰላለፍ በቀኝ ክንፍ ጀነራል ቪቶርዮ ዳቦርሜዳ የሚመራው ጦር በመሐከል በጀነራል ጁሴፔ አሪሞንዲ የሚመራው ጦር እንዲሁም በግራ ክንፍ ጀነራል በማቴዎ አልቤርቶኒ የሚመራው ጦር ሆኖ በጀነራል ጁሴፔ  ኤሌና የሚመራው ተጠባባቂ ጦርና ጠቅላይ አዛዡ ጀነራል ባራቲዮሪ ደጀን በመሆን ተዘጋጅተው ነበር::

የኢትዮጵያ ሠራዊት  አሰላለፍ ደግሞ ከአድዋ በስተደቡብ ቀኙን ክንፍ ንጉስ ተክለሃይማኖት ሲይዙ መሃል ራስ መኮንን ሶሎዳ ተራራን መሃል አድርገው በግራ ክንፍ ራስ ሚካኤልና ራስ መንገሻ ጦራቸውን አሰልፈው ነበር:: ከአድዋ በስተጀርባ ደጀን የሆኑት ንጉሰ ነገሥቱ እቴጌ ጣይቱና ራስ ወሌ ሲሆኑ ራስ አሉላና ፊትአውራሪ ገበየሁ በግራና በቀኙ አቅጣጫ ከፊት ቀድመው ተሰልፈው ነበር::

ባራቲዮሪ ድንገት ለማጥቃት አቅዶ ስለነበር በየካቲት 22 ምሽት ጣልያኖቹ እንቅስቃሴ ጀመሩ:: ይሁንና ይህ ዕቅድ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ቀድሞ ታውቆ ነበር:: ለኢጣልያ ያገለግሉ የነበሩና የእንጢቾው ባሻ አውአሎም የተባሉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይህንን የጣሊያኖቹን የጦር ዕቅድ ለራስ መንገሻ ወይንም ራስ አሉላ ስለነገሩ ጉዳዩ ለአጤ ምንሊክ ተነግሮቸው ነበር ይባላል::

ይሁንና ጣልያኖቹ ጎህ ሲቀድ በየካቲት 23 እለት ጥቃት ሰነዘሩ:: በመድፍ ተኩስ ልውውጥ የተጀመረው ፍልሚያም እየጋለ ሄዶ የጠመንጃ ተኩስ የበረታበት ካባድ ግርግር ሆነ:: በዚሁ ጦርነትም ከባድ ጉዳት ደረሰ:: በጣሊያኖቹ በኩል 261 መኮንኖች 2,918 ወታደሮች እና በግምት 2,000 አስካሪ ወታደሮች (የኤርትራ ተወላጆች) ሲሞቱ 954 ኢጣሊያዊያን የገቡበት ጠፋ 471 ኢጣሊያውያንና 959 አስካሪ ወታደሮች ቆሰሉ.. ይህም ማለት ጣልያኖቹ ካሰለፉት ጠቅላላ ሠራዊት 43% ያህሉን አጡ:: ከአምስቱ ታላላቅ የጦር መሪዎቻቸው መካከልም ሁለቱ (አርሞንዲና ዳቦርሜዳ) ሲገደሉ ሶስተኛው (አልቤርቶኒ) በኢትዮጵያውያን ተማረከ:: ከጦር ሜዳው እግሬ አውጪን ያሉት ጣልያኖችም መድፎቻቸውን በሙሉ እንዲሁም 11,000 ጠመንጃዎችና የመጓጓዣ መሣሪያዎቻቸውን ጥለው ነበር::

 

የአድዋ ድል ለወጣቱ ትውልድ ያለው እንድምታ በገዛኢ ሀይለ

ለነፃነት እና አንድነት

በጦርነቱ ወቅት የታየው የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተሳትፎ አለም አቀፉን ማህረሰብ ያስደመመ ትእይንት ነበር፡፡ የአድዋ ድል የኢትዮጵያን ነፃነት ከማስከበር ባሻገር ብሄራዊ ስሜትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎለብትና ስር እንዲሰድ አብይ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡  ይህም በወቅቱ የተለያየ ፍላጎትና ጠብ የነበራቸው ያካባቢ  መሪዎች ለሀገራቸው ነፃነት ሲሉ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ ዘምተዋል ፡፡

ለሰላምና ለመልካም ግንኙነት የተከፈለ ዋጋ

የተምታታውን የውጫሌ ውል ከመሰረዛቸው በፊት አፄ ሚኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ የተሳሳተውን ትርጉምና የኢትዮጵያን መንግስት ለማታለል የተጠነሰሰውን ሴራ እንዲስተካከል ካውንት አንቶነሊን ጠይቀውታል፡፡ ከዛም ለሰላም ያላቸው ፍላጎት ሰሚ በማጣቱ እናም ትእግስታቸው በማለቁ እቴጌ ጣይቱ እንዲ በማለት መልስ ሰጥተዋል፣

ፍላጎትዎ ከሆነ ጦርነቱን በሚቀጥለው ሳምንት መጀመር ትችላላችሁ፡፡ ማንም ሰው አይፈራችሁም፡፡ወደ ተግባር ስትገቡ እናያችኋለን፡፡ እኛ ለሀገራችን ምቾታችንን እና እንደማንሰጥ አድርጋችሁ እንዳታስቡ፣ ለሀገርህ መስዋእት መሆን ታላቅ ክብር ነው፡፡ እናንተን እዚህ ማየትም ሆነ ማቆየት አልፈልግም ምክንያቱም አገሬ በጨለማ ትዋጣለችና፡፡ አላማችሁን ወደ ተግባር ከማሸጋገራችሁ በፊት ብዙ ብታስቡበት መልካም ነው፡፤ ጦርነት ባልመርጥም የእናንተን ውል ከመቀበል ሞትን እመርጣለው፡፡

በዚህ መልኩ ሰላም ባይመጣም ለመልካም ግንኙነት የተከፈለው ዋጋ ታላቅ ነበር፡፡

የአድዋ ድል ሌሎች እንደሚያስቡት ከመቅፅበት የመጣ አይደለም፡፡ የአድዋ ድል ዘርፈ ብዙ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አሰራሮችና ልምዶች ውጤት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ድል በቀኝ ግዛት የነበሩት አገራትና ህዝቦች ከሰጠው ትምህርት ባሻገር ለሰው ልጆች መብትና ነፃነት መከበር የማይከፈል መስዋእት እንደሌለ ለአውሮፓ ወራሪ ሀይሎች ያስተላለፈው መልዕክት ጉልህ ሚና ነበረው፡፡ የአውሮፓ ወራሪ ሀይሎች ወደ አፍሪካ የመጡት ወንድም ህዝብን ራሱን በራሱ በመከፋፈልና በማጋጨት እንዲሁም ባህሉን ረስቶ የነሱን ባህል እንዲይዝ በማድረግ የአጉሩን ሀብት ለመበዝበዝ እንጂ ከአፍሪካ ህዝብ ጋር ወዳጅነት ለመመስረት እና ለጋራ ጥቅም |አብሮ ለመስራት እንዳልሆነ በአድዋ ድል ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ይህን በቅጡ የተረዱ የአፍሪካም ሆነ የሌላው ዓለም ጭቁን ማህረሰብ ከኢትዮጵያ ሁሉ አለም አቀፍ ትምህርት በመውሰድ ፀረ ቅኝ ግዛት ትግላቸውን ተያይዘው ከኢትዮጵያ ጋርም አብረው ሰርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለፀረ ቅኝ ግዛት ባደረገችው ትግል የፓን አፍሪካ ማዕከልና አንቀሳቃሽ ሞተር ለመሆን በቅታለች፡፡

በአድዋ ድል ሳብያ አገራችን በአለም መድረክ ላይ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘችበት ሁኔታ የተፈጠረላት ሲሆን፣ ቀደም ሲል ዕውቅናውን አንሰጥም ሲሉ የነበሩ የአውሮፓ መንግስታት ሁሉ ለሀገራችን እውቅናን በመስጠት ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ላይ መክፈት የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡

ይህ ታሪካዊ ክስተት አድዋን ብሎም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በአለም ደረጃ ያስተዋወቀና ጎልቶ የወጣ የታሪክ አሻራ  በመሆኑ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለጥቁሩም አለም የኩራት ምንጭ ሆኖ ሲንፀባረቅ የሚኖር ዘላለማዊ ቅርስ ነው፡፡

ከ አድዋና አፍሪካ መፅሀፍ የተወሰደ ( እ.ኤ.አ 2002 እትም)

በዛሬው እለትም 121ኛውን የድሉን በዓል በምንሊክ አደባባይ እና ሌሎች ቦታዎች በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል፡፡

picture by: Abinet Teshome
http://instagram.com/ab_onthestreet
picture by: Abinet Teshome
http://instagram.com/ab_onthestreet
picture by: Abinet Teshome
http://instagram.com/ab_onthestreet
picture by: Abinet Teshome
http://instagram.com/ab_onthestreet
picture by: Abinet Teshome
http://instagram.com/ab_onthestreet
picture by: Abinet Teshome
http://instagram.com/ab_onthestreet

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.