በአድዋ የታየው የመቻቻልና የመተሳሰብ ብልሃት ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይሠራ ይሆን?

0
926

በፍቃዱ አለሙ

በዓለም ላይ ከተመዘገቡት ታላላቅ ታሪኮች መካከል የአድዋ ታሪክ አንዱ ነው፡፡ ይኽም በዓለም ታሪክ የተለየና ያልተለመደ ነው፡፡ በታላቅ ድል አድራጊነት የሚታወቁትን ሮማውያን በአድዋ ተራሮች ላይ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን በነጭ ላይ የነገሡበት የነጻነት ክብር ነው አድዋ፡፡ ብዙ የውጭ ጸሐፍት በዚህ የድል ምስጢራዊነት እንደ ተገረሙ ይኖራሉ፡፡ ምስጢር ምስጢር ነውና፡፡ በርግጥ አባቶቻችን ይሄን ምስጢር ለእኛ ሳይፈቱልን አላለፉም፤ ማስተዋል ካለ ሁሉም በጊዜውና በሱባኤው ተገልጧል፡፡

የአድዋ ድል ከድንበር ሉአላዊነት ጋር ተያይዞ የሚዘከር የነጻነት፣ የኩራትና የክብር በዓል ብቻም አይደለም፡፡ በመላው አትዮጰያዊ ብሎም በአፍሪካና በዓለም ታሪክ የሚታወቀው የጥቁር ሕዝብ ድል የሆነው የአድዋ ድል ትርጉም ብዙ ያልተጠበቁ ውጤቶችን አምጥቷልና፡፡ ከሀገር ውስጥ ብንጀምር ከነጻነትና ከኩራት ባሻገር ቀደም ሲል በዘመነ መሳፍንት የተሸነቆረውን ካባቢያዊ ሽኩቻ ወደ ኋላ በማሽቀንጠር ለዛሬ ማንነታችን መንገድ የጠረገ የመቻቻልና የመተሳሰብ ውጤትም ነው የአድዋ ታሪክ፡፡  በዚኽ ሂደት እምዬ ምኒልክ ዐራት ታላለቅ የታሪክና የትውልድ ድልድዮችን ገንብተው አልፈዋል፡፡

አንደኛው፡ በዘመነ መሳፍንት ተቆራርሳ የነበረችውን አትዮጵያ አንድ በማድረግ የዐፄ ቴዎድሮስን ኅልም ማከናወን ነበር፡፡ ለብዙዎቻችን ይሄ ሥራ ቀላል ይመስለናል ነገር ግን የሀገራችንን የታሪክ ቡግንጅ በደንብ ለተረዳ የእምዬ ምኒልክ የቤት ሥራ ምን ያኽል ከባድ እንደነበረ መረዳት አያዳግትም፡፡

ኹለተኛው፡ “ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ የአድዋ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የውስጥ ሽኩቻን ትቶ በመቻቻልና በመደማመጥ ለአንድ አላማ መሰለፍ እንዲችሉ አድርገዋል፡፡ ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ ሁሉም በየአካባቢው የተለያየ አመለካከት ይዞ ነበር…..ነገር ግን ሁሉም ለግዜው ይዞት የነበረውን አመለካካት ደምስሶ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንዲሰለፍ ከፍተኛ ጥበብ አሳይተዋል፡፡ ዐፄ ምኒልክ  ስለመተሳሰብና ስለመቻቻል የሰብኩ የመጀመሪያው ንጉሠ ኢትዮጵያ ናቸው፤ ያውም በዓለም ከሚነገርለት የኔልሰን ማንዴላ ትርክት ቀዳሚ ናቸው፡፡  ይህም ትርክት በአድዋ ጦርነት ላይ ተደግሟል…..ስለጦርነቱ አሰላለፍና ውሎ ከእቴጌ ጣይቱንና ከመኳንንቱ ጋር በመደማመጥና የሌሎችን አሳብ ከቁም ነገር በመቁጠር የመያኽላቸው አልነበረም፡፡ ጸሐፊው “ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥትና መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ፡፡ ” እንዲል

ሦስተኛው፡ ከኢትዮጵያ አልፎ ነጮች ለጥቁሮች የነበራቸውን ዝቅ ያለ ግምት ወይም የተንሸዋረረ አመለካከት እንዲያስተካክሉ አድርጓል፡፡ የዚህ ውጤት ለመላው ጥቁር አፍሪቃውያን ወገኖቻችን የነጻነት ጎህ ቀዶላቸዋል፡፡

ዐራተኛው፡ ከአድዋ ማግስት በነበረው የጥልያን ወረራ በልበ ሙሉነትና በኩራት የታጀበው የአርበኞች ድል የተገኘው ቀደም ሲል የነበረው የአድዋ መንፈስና ዝና በአርበኞቻችን ሥጋና ነብስ ተዋህዶ ስለነበር የትውልድ ቅብብሎሹን ማስቀጠል ችለዋል፡፡

ታዲያ ጥያቄው አድዋ ላይ ላስመዘገብነው የነጻነት ድል ቁልፉ በእንድነት ላይ የተመሠረተ የመቻቻልና መተሳሰብ ምስጢር ለምን ሀገራችን ኢትዮጵያን ከተጸናወታት የዘመኑ በሽታ መዳኅኒት ሆኖ አይፈውሳትም ነው፡፡ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የተለያየ አመለካከታቸውን ትተው በአንድ እንዲሰለፉ ያደረጋቸው የሀገር ፍቅርና ስሜት እንጂ ሌላ እንድም ጥቅም አልነበራቸውም፡፡ ያለፉት ኢትዮጵያውያን ከከባቢያዊ ትልማቸው ይልቅ ለታላቋ ሀገራቸው ደማቸውንና አጥንታቸውን የሰጡት ከሰውነት በላይ ትረጉም ላለው የሀገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ወላይታው፣ ጉራጌው፣ ጋምቤላው፣ አማራው  ሌላውም የኢትዮጵያ ክፍል ወደ አድዋ የዘመተው ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ነጻነት፣ ሉአላዊነት ከፍ ሲል የዚች ሀገር ባለቤቶች ሁላችን እንድንሆን ነው፡፡

በእርግጥ በአንድ ሀገር ብሔር፣ ብሔረሰብ ውስጥ አይደለም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ያ ቤተሰብ ቤተሰብ ሆኖ የሚዘልቀው ልዩነቱን ትቶ ሳይሆን አንድነቱ ላይ በማተኮርና ልዩነቱ ቤተሰቡን እንዳይበክለው ግለሰባዊ አመለካከቶች ከግለሰቦች የዘለለ ሚና እንዲይኖራቸው በማድረግ ነው፡፡ የአድዋን ድልና መንፈስ ስናስብ ቀድሞ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ያ ኢትዮጵያዊ አንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ከሆነ ወደ ቀደመው ክብራችን እንመለሳለን፡፡ እናም የአድዋን ዝክር አበባ ጉንጉን ከማስቀመጥ በዘለለ የአድዋን ድል የሚሰብክና በሰው አእምሮ ውስጥ ታትሞ የሚቆይ ምልክት ስናቆም ብቻ ነው፡፡

 

በተለይ ቀን ከሌት ሽንፈቱ የውርደት ጽዋ ሆኖ ይተናነቃቸው የነበሩት ጣሊያኖች ለሁለተኛ ጊዜ  ሀገራችንን ሲወርሩ ከአድዋ ማግስት ተወልደው ያደጉት የያኔው አርበኛ አባቶችና እናቶች በአድዋ መንፈስና ዝና ተኮትኩተው አድገው ዳግም ጥሊያንን ድል የማድረጋቸው ምስጢር የዚህ ዘመን ወጣት በደንብ ሊዋህደን ይገባል፡፡ ከእኛነታችን ይልቅ የእኛን ማንነት ያስከበረችልንን ሀገራችንን ልንወድ ይገባል፡፡ በአድዋ ዱር ገደል የወደቁት አባቶቻችን እና እናቶቻችን በውርደት ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል ብለው ነው፡፡ የሀገር አንድነትና ስሜት ልእልናው እጅግ ከፍ ያለ ነው፤ ከእኔ ሀገሬ ይበልጣል የሚል፡፡

ስለዚህ ይህ የአድዋ መንፈስና ዝና በእኛ ትውልድ ሥራውን እንዳያቆም ከእኛ ይልቅ ቅድሚያ ለሀገሬ የሚል መንፈስ በውስጣችን አንገንባ፡፡ ከእኛ ክብር ይልቅ የሀገራችን ክብር ከፍ እናድርግ፡፡ ከቻልን “ጉዞ  አድዋ” እንደተሰኘ ዓይነት የጉዞ መርሐ ግብር በመሳተፍና ሕብረቱ እንዲስፋፋ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ፡፡ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችንን አጥንታቸውን የከሰከሱበትንና ደማቸውን ያፈሰሱበትን አድዋ (የሶሎዳ) ተራራ ሄዶ በመጎብኘትና በማጥናት የአድዋውን መንፈስና ዝና በልባችን መጣፍ እንችላላንና፡፡ አንዳንዴ በመማርና በመስማት ብቻ የመጣ ትውልድ የታሪኩን አሻራና ዋጋ ሊረዳው አይችልም፡፡  ኢትዮጵያችን ለሁላችን በልካችን ተሠርታ ተሰጣናለች እናም ከቻልን አናጥብባት ወይ መካን አናድርጋት፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.