የአእምሮ ማጎልመሻ የጥንት ባህላዊ ጨዋታዎች

0
1612

የአእምሮ ማጎልመሻ የጥንት ባህላዊ ጨዋታ

እነዚህ ከታች የምታዩዋቸው ጨዋታዎች በድሮ ጊዜ በኢትዮጵያ በተለምዶ ይጫወቷቸው የነበሩ ጨዋታዎች ሲሆኑ አእምሮን ያጎለምሳሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

1.የገበጣ ጨዋታ

የገበጣ ጨዋታ ምንም ያልተቀላቀለበት ንፁህ የኢትዮጵያ ጨዋታ ነው፡፡ የገበጣ ጨዋታ መች እንደተጀመረ በትክክል ለማወቅ ያሰቸግራል፡፡ እኔ ተወልጄ በአደግሁበት አካባቢ በየቤቱ ብቻ ስይሆን በየጫካው በትልልቆች አለቶችና ቋጥኞች ላይ የሚገኙት የገበጣ መጫወቻ ጉድጓዶች አጠገብ ላይ ትልልቅ ዛፎች በቅለውባቸው በጫካ ተውጠው ይታያሉ፡፡ ይኸውም የሚያሳየው የገበጣ መጫወቻ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ባህላዊ ጨዋታ መሆኑን ነው፡፡

 

የገበጣ መጫወቻ ዋና መደብ ከእንጨት ተጠርቦ የተዘጋጀ ወይም ከሚንቀሳቀስ ድንጋይና ከማይንቀሳቀስ ዐለት ተወቅሮ የተዘጋጀ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእንጨት እና ከተንቀሳቃሽ ድንጋይ የሚዘጋጀው የገበጣ መጫወቻ የሚታጠፍ እና የሚዘረጋ ወይም የማይታጠፍ እና የማይዘረጋ ሊሆን ይችላል፡፡

የገበጣ መጫወቻ ጉድጓዶች በመሰረቱ 18 መሆን ይገባቸዋል፡፡ ቢሆንም በ12 ጉድጓዶችም ለመጫወት ይቻላል፡፡

የገበጣ ጨዋታ ተጋጣሚዎች በመሰረቱ ሁለት ሰዎች ብቻ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በ18 ጉድጓድ መጫወቻ ላይ ግን 3 ሰዎችም ሆነው ለመጫወት ይችላሉ፡፡

የገበጣ መጫወቻ ጠጠሮች ድቡልቡል ድንጋዮች ወይም ድቡልቡል የዛፍ ፍሬዎች ወይም ለዚሁ ተብለው ከእርሳስ ወይም ከብር የተሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የጥንት መኳንንቶች ግምጃ ቤቶች የሚተሳሰቡትም ግብጦ በምል መጠርያ ከዚህ በላያ በተባሉት የገበጣ መጫወቻ ጠጠሮች ነበር፡፡ ይተሳሰባሉ ይጋበጣሉ፡፡ ሂሳብ ይወራረዳሉ ይጋበጣሉ ይባል ነበር፡፡ ገበጣ የሚለው ቃል ሂሳብ ማለት ይመስላል፡፡ ግን ቃሉ ከጥንታዊነቱ የተነሳ ትርጉሙ ይህ ነው ብሎ ለማስረዳት ያስቸግራል፡፡

በሌላ በኩል በየገበጣው ጉድጓድ ውስጥ የሚቀመጡት ጠጠሮች ሦስት ሦስት ወይም አራት አራት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መደበኛ ዋናው ጨዋታ ግን ሦስት ጠጠር በየጉድጓዱ በማስቀመጥ ነው፡፡

 

 

2.የሠንጠረዥ ጨዋታ

በኢትዮጵያ ቤተ መንግስትና በየመኳንንቱ አካባቢ የተለመደ ነበር እየተባለ ይነገራል፡፡ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የውጭ ሀገር ሰዎችም የሠንጠረዥ ጨዋታ በኢትዮጵያ እንዴት እንደነበር ጽፈዋል፡፡

የሠንጠረዥ ጨዋታ በአለም የታወቀ ሲሆን ከህንድ ወደ ፐርሲያና ወደ አረቦችም ከዛም ወደ ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ተስፋፋ ይላሉ፡፡

በ1959-1960 ዓ.ም በአክሱም ከተማ ወደ ሽፌ በሚወስደው መንገድ አጠገብ በተገኘው የከተማ ፍራሽ ከአውሮፓ የመጡት አርኪዮሎጅስቶች እያስቆፈሩ ያገኙዋቸው የጥንት ልዩ ልዩ እቃዎች የአንድ አዳራሽ ደረጃና ከሸክላ የተሰራ የዳቦ መጋገርያ በምያሳዩኝ ጊዜ ሁለት ከአመትስት ድንጋይ የመሳሰሉ በአራት መአዘን ደንበኛ CUBE መጫወቻ አግኝተው አሳይተውኛል፡፡

በግእዝ፤ ትግርኛ አማርኛ ለጊዜው ስሙን የማላውቀው በጀርመንኛ WURFEL በእንግሊዝኛ  CUBE በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከነበሩት ጨዋታዎች በረዥሙ የታሪክ ጉዞና በልዩ ልዩ ምክንያቶች አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ጨዋታዎች ጠፍተው እንደቀሩ ልንረዳ እንችላለን፡፡

 

እነዚህ የመጫወቻ እቃዎች በጀርመንኛ WURFEL በእንግሊዝኛ  CUBE የሚባሉት ናቸወ›› እነዚህ እኔ በአክሱም ከተማ በአይኔ ያየኋቸው እቃዎች አራት መአዘን ሆነው በሚገባ የተዘጋጁ ሲሆኑ ከአንድ እስከ ስድስት ነጥብ ያላቸው ናቸው፡፡ ይኸውም የሚያመለክተው በጥንት ጊዜ በኢትዮጵያ በቆዳ ዋንጫ ውስጥ እየከተቱ በመድፋት ሲጫወቱበት የነበሩ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ የመጫወቻ እቃዎች ባይገኙ ኖሮ በድሮ ጊዜ በኢትዮጵያ የህ አይነት ጨዋታ የነበረ መሆኑን ለማሰብ ባልቻልን ነበር፡፡

 

 

  1. ጉሮ በሸዋ አማርኛ አካንዱራ

 

የጉሮ ውግ አካንጉራ ጨዋታና ውድድር በኢትዮጵያ የተለመደ ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ ወንዶች ወጣቶች በክረምት ወራት የሚጫወቱት ነው፡፡ ጉሮ የተባለው የመጫወቻ መሣሪያ የሚሰራው ከበሬ ወይም ከላም ጎድን አጥንት ሲሆን አጥንቱ ጠሰንጥቆ ተጠርቦ ይለዝብና በአንድ በኩል ሹል ሆኖ በሌለ በኩል ደግሞ ሰፋ ብሎ ይዘጋጃል ፡፡ ጉሮ በተባለው የአጥንት ሹል እየወጉ የሚወዳደሩበት ደግሞ የጉሎ ለስላሳ ለበቅ ወይም ሌሎች ለስላሳ ቡቃያዎች በቀላሉ የሚወጉ ለበቆች ተቆርጠው በትክክል ይከረከማሉ ፡፡ እነዚህ ለስላሣ ለበቆች በተርታ ተሰተካክክው በግራ መዳፍ እጅ ከታች ጣቶችን በማስደገፍ ይያዛሉ፡፡ ተወዳዳሪዎቹ በቀኝ እጆቻቸው ጉሮ የተባለውን እያፈናጠረ በግራ እጁ በተርታ የተያዙትን ለበቆች በተራ ሳይስት ለመውጋት ይሞክራል፡፡ አሸናፊ እና ተሸናፊው የሚታወቀው በሚያደርጉት ውግ ስሌት መሠረት ነው፡፡

 

  1. ሐንዳይ ድቡሽ

የድቡሽ ጨዋታ የውድድር ጠባይ ያለው በኢትዮጵያ የተለመደ ጨታ ነው፡፡

ይህ ጨዋታ አብዛኛውን ጊዜ የልጃገረዶች ጨዋታ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ወንዶች ልጆችም አብረው ይጫወቱታል፡፡

የድቡሽ ጨዋታ በድቡልቡል ጠጠሮች ሲሆን የተወሰነ ቁጥር እንዳለው አላውቅም፡፡ በመዳፍ እጅ ጨብጠው የያዝዋቸውን ጠጠሮች ወደ ላይ ወርውረው እንዳሉ በሙሉ በመዳፍ እጅ ጀርባ ማሳረፍና አሁንም ሳይወድቁ እንዳሉ ወደ ላያ ወርውሮ በመዳፍ እጅ መቀበል አሸናፊ ማን እንደሆነ የሚገመተው በስሌት ነው፡፡

 

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.