በአፍሪካ ዋንጫው ምክንያት የትኞቹ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በይበልጥ ይጎዳሉ?

0
1022

31ኛው የጋቦን አፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረ ሳምንት ሆኖቷል። በዚህ ውድድር በአጠቃላይ 21 ተጨዋቾች ከ13 የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ሃገራቸውን ለመወከል ጋቦን ተገኝተዋል። ቀጣዩ አጭር ጥንቅርም በዚህ ምክንያት ‘የስኳድ’ መሳሳት የሚያጋጥማቸው ክለቦች የትኞቹ እንደሆኑ ይነግረናል።

1. ዌስትሃም ዩናይትድ እንደ ለንደኑ ክለብ ዌስትሃም ይህ የአፍሪካ ዋንጫ የሚጎዳው ክለብ እንደሌለ ዕለታዊው ‘ዘ ሰን’ ጋዜጣ ያስነብባል። በውድድር አመቱ መጀመሪያ መልካም አቋም ላይ ያልነበረውና በሂደት ከወራጅ ቀጠና መውጣት የቻለው የስላቪያን ቢሊች ቡድን 4 ያህል ተጫዋቾቹን በአህጉራዊው ውድድር ምክንያት የሚያጣ ሲሆን እነርሱም; አንድሬ አየው (ጋና)፣ ሶፊያን ፊጎሊ (አልጄሪያ)፣ ቼኩሁ ኮያቴ እና ዲያፍራ ሳኮ ( ሴኔጋል) ናቸው።  አልጄሪያዊው ፊጎሊ በመጨረሻም ከብ/ቡድኑ ምርጫ ውጪ በመደረጉ ከክለቡ ጋር መቆየት ችሏል።

2. ሰንደርላንድ በወራጅ ቀጠና ለሚገኘው ሰንደርላንድ ምናልባትም ይህ የአፍሪካ ዋንጫ አሰልጣኙን ዴቪድ ሞዬስን በጥር የተጫዋቾች ዝውውር ገበያ እንዲወጡ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ጥቋቁር ድመቶቹ የአራት ያህል ተጫዋቾችን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን ፓፒ ዴላቡጂ (ሴኔጋል)፣ ዋህቢ ካዝሪ (ቱኒዝያ)፣ ላሚን ኮኔ (አይቮሪኮስት)፣ ዲዲዬ ንዮንግ (ጋቦን) ከሃገራቸው የደረሳቸውን ጥሪ አክብረው ጋቦን የተገኙ የሰንደርላንድ ተጫዋቾች ናቸው። * ፓፒ ጄላቡጂ ከቶታል አፍሪካ ዋንጫ የሴኔጋል ቡድን የመጨረሻ ምርጫ ውጪ በመደረጉ ለክለቡ ግልጋሎት መስጠቱን ቀጥሏል።

3. ክሪስታል ፓላስ ወደ ወራጅ ቀጠና እየተንደረደረ የሚገኘውና ባጋጠመው የውጤት ቀውስ አሰልጣኝ አለን ፓርዲውን በማሰናበት የቀድሞ የእንግሊዝ ብ/ቡድን አሰልጣኝ የነበሩትን ሳም አላርዳይስን የቀጠረው ፓላስ ለአይቮሪኮስት ለመጫወት የወሰነውን ዊልፍሬድ ዛሃን ማጣቱ በእጅጉ ይጎዳዋል። ኩዊንሲ አፒያ (ጋና) እና ባካሪ ሳኮ (ማሊ) የክለባቸውን ቁልፍ ተጫዋች ተከትለው ወደ ጋቦን የበረሩ ሆነዋል።

4. ሌስተር ሲቲ የአምናው አስገራሚ የሊግ ባለድልና በዘንድሮው ውድድር የሊጉ ወገብ ላይ በመቀመጥ የወራጅነት ስጋት ያንዣበበት ሌስተር የሁለቱን አልጄሪያውያን ሪያድ ማህሬዝና ኢስላም ሲሊማኒን ግልጋሎት ማጣቱ የውጤት ማጣቱን ቀውስ እንዳያባብስበት ተሰግቷል። ከእነርሱ በተጨማሪ አዲሱ ፈራሚያቸው ዳንኤል አማርቴ ለጥቋቁር ኮከቦቹ ጋና ለመጫወት ወደ ጋቦን ያቀና ሌላው የሌስተር ከተማ ተጫዋች ሆኗል።

5. ሊቨርፑል ለሊጉ ዋንጫ ቼልሲን በቅርብ ርቀት እየተፎካከረ ለሚገኘው ሊቨርፑል የሴኔጋላዊው ሰኢዶ ማኔ አለመኖር ምናልባትም ጀርመናዊውን አሰልጣኝ የርገን ክሎፕን በጥር ወር ‘ለብቻቸው የሚራመዱ አይነት’ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይታሰባል ሲሉ የእግር ኳስ ተንታኞች ሹፈት አዘል ሃሳብን ይሰነዝራሉ። ዘንድሮ ለዋንጫ ከተጠበቁት ሃገራት ተርታ የሆነችው ሴኔጋል ሁለቱን ተከታታይ የምድብ ጨዋታዎቿን ቱኒዝያንና ዚምቧቡዌን በተመሳሳይ 2-0 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን በማረጋገጧ የርገን ክሎፕ በወሩ መጨረሻ ከቼልሲ ጋር የሚያደርጉትን ወሳኝ የአንፊልድ ፍልሚያ ጨምሮ በቀሪ ጨዋታዎች ማኔን እንደማያገኙ ተረጋግጧል።

6. ዋትፎርድ በጫና ውስጥ የሚገኙት ጣልያናዊ ዋልተር ማዛሪ የሊጉን የጥር ወር መርሃ ግብር በመልካም ጎኑ ላይመለከቱት እንደሚችሉ መናገር ይቻላል። ለዚህም ምክንያቱ 3 ተጫዋቾቻቸውን ወደ ሚወክሏቸው ሃገራት መላካቸው ሲሆን እነርሱም ኖርዲን አምራባት (ሞሮኮ)፣ ብሪስ ጃ ጄጄ (አይቮሪኮስት) እና አድሊን ጉዋዲዮራ (አልጄሪያ) ናቸው። አምራባትን ጨምሮ እንደ ሶፊያን ቡፋል (ሳውዝአምፕተን) የመሳሰሉ ወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከሞሮኮ ቡድን ውጪ ተደርገዋል።

ማጠቃለያ:- የአፍሪካ ዋንጫ ሚካሄድበት የጊዜ ካላንደር ከአውሮፓ ሊጎች ጋር መጋጨቱ የውድድሩን ጣዕም ቀንሶታል የሚሉ ተከራካሪዎች ቢበዙበትም የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ ‘ካፍ’ ከግዙፉ የፈረንሳይ ነዳጅ እና ጋዝ አምራች አለምአቀፍ ኩባንያ ቶታል ጋር የፈፀመው የ1 ቢሊዮን ዶላር ስፓንሰርሺፕ ስምምነት ( ለ3 አመታት በካፍ ስር የሚደረጉ ማናቸውንም ውድድሮች ያካትታል) በጋቦኑ ውድድር ለአሸናፊዎች የሚሰጥ ክፍያን ከፍ ማድረጉ በውድድሩ የፉክክር መንፈስን ሊጨምር እንደሚችል በመጥቀስ ጣዕሙ እንዳልቀነሰም የሚሞግቱ አልታጡም።

የአፍሪካ ዋንጫ ዋና ዋና እውነታዎች

• ግብፅ የውድድሩ በጣም ስኬታማዋ ሃገር ስትሆን በአጠቃላይ 7 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን በታሪክ ቀዳሚዋ ሃገር ናት። ‘ፈርኦኖቹ’ 3 ተከታታይ አፍሪካ ዋንጫዎችን( 2006፣08፣10) ካሸነፉ በኃላ ያለፉትን 3 ተከታታይ ውድድሮች ማጣሪያውን ማለፍ አለመቻላቸው አነጋጋሪ ሆኖ ነበር..

• ካሜሮናዊው ሳሙኤል ኤቶ 18 ጎሎችን በማስቆጠር የአፍሪካ ዋንጫው የምንግዜም ኮከብ ግብ አስቆጣሪነትን በአንደኝነት ይመራዋል።

• ግብፃዊው የ43 አመት ግብ ጠባቂ ኢሳም ኤል ሃዳሪ በዕድሜ አንጋፋው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ሲሆን በአንድ ወቅት በአይቮሪኮስታዊው አጥቂ ዲዲዬ ድሮግባ ሳይቀር በተቃራኒ ከገጠምኳቸው ምርጡ በሚል እንደተሞካሸ ይነገራል።

• የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ እ.ኤ.አ 1957 በ 3 ሃገራት መካከል የተካሄደ ሲሆን እነርሱም ሃገራችን ኢትዮጵያ፣ ጎረቤት ሱዳንና ግብፅ ሲሆኑ 4ኛዋ ሃገር ደ/አፍሪካ በአፓርታይድ ስርዓት ምክንያት ራሷን አግልላ ነበር።

• ጊኒ ቢሳው በ31ኛው ቶታል አፍሪካ ዋንጫ የምትቀርብ ብቸኛዋ እንግዳ ሃገር ናት።

በ31ኛው ቶታል አፍሪካ ዋንጫ እስካሁን

• አስተናጋጇ ጋቦን፣ ጊኒ ቢሳው እና ዩጋንዳ ተሰናብተዋል
• የተመልካች ድርቅ በስታዲየሞች በስፋት ተስተውሏል
• ሴኔጋል በቀድሞ ተጫዋቿ አሊዩ ሲሴ እየተመራች ለዋንጫው ቀዳሚ እጩ ሆናለች
• የቴሌቪዥን ሽያጭ ውድነት ውድድሩ ብዙሃን በቤታቸው በቲቪ መስኮት እንዳይመለከቱት ሆኗል
• 34 ግቦች በ18 ጨዋታዎች ከመረብ አርፈዋል
• ክሎድ ሎርዋ በአፍሪካ ዋንጫው ለ9ኛ ጊዜ በአሰልጣኝነት በመቅረብ ባለሪከርድ መሆን ችለዋል
• በአጠቃላይ ውድድሩ ሳቢና ማራኪ እግር ኳስ ያልታየበትም ተብሏል!!

በረከት ፀጋዬ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.