31ኛው ቶታል አፍሪካ ዋንጫ በጋቦን አስተናጋጅነት ሊጀመር የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል::

0
869

 

31ኛው ቶታል አፍሪካ ዋንጫ በጋቦን አስተናጋጅነት ሊጀመር የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል። ቀጣዩ አጭር ጥንቅር 16 ሃገራት በ 4 ምድብ ተከፍለው የሚያካሂዱትን ውድድር ምድብ በ ምድብ ይዳስሳል።

  • ግሩፕ A- ጋቦን, ካሜሮን, ቡርኪናፋሶ, ጊኒ ቢሳው
  • ግሩፕ B አልጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ፣ዙምባቡዌ
  • ግሩፕ C አይቮሪኮስት፣ሞሮኮ፣ዲ. ኮንጎ፣ቶጎ
  • ግሩፕ D- ግብፅ፣ጋና፣ማሊ፣ዩጋንዳ

 

ግሩፕ A ጋቦን, ካሜሮን, ቡርኪናፋሶ, ጊኒ ቢሳው

ጋቦን:-

አስተናጋጇ ሃገር ጋቦን ከከዚህ ቀደሙ በተሻለ ወደ ሩብ ፍፃሜ ልትሻገር የምትችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን መናገር ይቻላል ሲል የቀድሞ ‘ሰንደይ ታይምስ’ ጋዜጣ አምደኛ የሆነው ጋዜጠኛ ኢያን ሃውኪ ይናገራል። በእርግጥ እ.ኤ.አ. 2012 ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር በጣምራ ባስተናገደችው ውድድርም ከምድብ ማለፍ ችላ የነበረ ሲሆን በንፅፅር ቡድኑ ከያኔው ይልቅ የአሁን ጥንካሬው ሚዛን የሚደፋ እንደሆነ ሃውኪ ይከራከራል። ለዚህም ዋናው ምክያት ግብ አዳኙ ፒዬር ሜሪክ ኦባሚያንግ በመልካም አቋም ላይ መገኘት እንደሆነ ሃውኪ ይጠቅሳል። ፈጣኑ ኦባሚያንግ በዘንድሮ የጀርመን ቡንደስሊጋ ለክለቡ ዶርትመንድ 13 ጨዋታዎችን ፈፅሞ 16 ግቦችን ከመረብ ያዋሃደ ከመሆኑ ባሻገር የሃገሩን ጥሪ ችላ ሳይል ለአፍሪካ ዋንጫው መጓዙ ለጋቦን ትልቅ ተስፋ ይሆናታል።

ካሜሮን:-

አህጉራዊ ክብርን ከግምት ከከተትን አሁንም የማይበገሩት አንበሶች ጠንካራ እንደሆኑ አንክድም። ይሁን እንጂ ብሄራዊ ቡድኑ በውስጡ ያለው ውጥረትና ( internal tension) በርካታ ‘ሲኒየር’ ተጫዋቾች ራሳቸውን ከቡድኑ ማግለላቸው ለቤልጀምያዊው አሰልጣኝ ሁጎ ብሩስ ራስ ምታት ከመሆን ባለፈ የቡድኑን ስብስብ እንዳመናመነው ተዘግቧል። የሊቨርፑሉን ተከላካይ ጆኤል ማቲፕን ጨምሮ እንደ ቼፖ ሞቲንግ ( ሼልከ 04) የመሳሰሉ ሰባት ያህል ከዋክብት ከብ/ቡድኑ የቀረበላቸውን ጥሪ ውድቅ ማድረጋቸው የ4 ጊዜ የአህጉሪቱ ሻምፒዮን ለሆነችው ሃገር ከምድብ የማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይከታት እሰጋለሁ ሲል ሃውኪ ፅፏል።

ቡርኪናፋሶ:-

ቡርኪና በቡድኑ የ2013 ቱን ስኬት መመለስ የሚችሉ ባለ ተሰጥኦ ተጨዋቾችን እንደያዘች ይነገራል። በደቡብ አፍሪካው የ2013 አፍሪካ ዋንጫ ለፍፃሜ መቅረብ ችለው የነበረ ቢሆንም በቀጣዩ 2015 ኢኳቶሪያል ጊኒ ውድድር ከምድብ የተሰናበቱበትን ውጤት ለመቀልበስ ተስፋን ይሰንቃሉ።

ጊኒ ቢሳው:-

ብቸኛዋ የአፍሪካ ዋንጫው እንግዳ ሃገር ስትሆን በምድቡ የሚሰጣትም ግምት አናሳ እንደሆነ ይታወቃል። በ2012 ሻምፒዮን የሆነችውን ዛምቢያን በልጠው ለውድድሩ መብቃታቸው በንቀት እንዳንመለከታቸው ምክንያት ይሆናል ሲል ጋዜጠኛ ኢያን ሃውኪ ‘ዘ ናሽናል’ ለተሰኘው ተነባቢ የመካከለኛው ምስራቅ ጋዜጣ ሃሳቡን ይሰጣል። (ይቀጥላል)

ግምት:- ጋቦን እና ቡርኪናፋሶ ከምድቡ ያልፋሉ!!

 

ግሩፕ B አልጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዝያ፣ዙምባቡዌ

 

አልጄሪያ:-

በአህጉሪቱ በእግር ኳስ ደረጃቸው ላቅ ያለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሃገራት በዚህ ምድብ መገኘታቸው ምድቡን የሞት ምድብ አስብሎታል። የወቅቱን የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋችነት ምርጫን ያሸነፈውና ሳይጠበቅ ሌስተር ሲቲ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን እንዲያነሳ ትልቁን ሚና የተጫወተው ሪያድ ማህሬዝ ሃገሩ አልጄሪያ በውጤት ጎዳና እንድትጓዝ ብዙ ይጠበቅበታል። ከማህሬዝ ባሻገር እንደ ኢስላም ስሊማኒ፣ ነቢል ቤንታላብ፣ ያሲን ቤራሂሚን የመሳሰሉ ከዋክብትን ያካተቱት የበረሃ ቀበሮዎቹ ምድቡን በበላይነት የመደምደም ቅድሚያ ግምትን አግኝተዋል።

ሴኔጋል:-

በወረቀት ላይ ሲታይ ‘የታራንጋ አንበሶቹ’ አስፈሪ ቡድን እንደያዙ መናገር ይቻላል። ሰኢዶ ማኔን በፊት መስመር ላይ ለምታሰልፈው ሃገር ምንም እንኳን ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ ጥሩ ባይሆንም በዚህኛው ውድድር ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ረጅም ርቀትን መጓዝ ታልማለች። ለዚህም የቀድሞ ተጫዋቿ የነበረውና አሁን ቡድኑን በማሰልጠን ላይ ከሚገኘው አሊዩ ሲሴ ብዙ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።

ቱኒዝያ:-

ባለፉት ተከታታይ የነጥብ ውድድሮች ላይ እንደገነቡት አይነት ‘ታክቲካል ዲሲፕሊንን’ የሚያስቀድም ቡድን ፓላንዳዊው ሄነሪክ ከስፐርዣክ መገንባት ከቻሉ ከአልጄሪያ ወይም ሴኔጋል አንዳቸውን ረግጠው ማለፍ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ጋዜጠኛ ኢያን ሃውኪ ይገምታል።

ዙምባቡዌ:-

ደቡባዊውን የአህጉሪቱን ክልል በብቸኛነት የምትወክለው ሃገር ምንም እንኳን በምድቡ አናሳ ግምት የሚሰጣት ሃገር ብትሆንም የወቅቱን የአፍሪካ የክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ማሸነፍ የቻለው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ማሜሎዲ ሳንዳውንስ የፊት መስመር ኮከብ ተጫዋች ካሚ ቢላትን በቡድኗ እንደመያዟ ቀላል ግምት መስጠት ዋጋ እንደሚያስከፍል መተንበይ ይቻላል።

ግምት:- አልጄሪያና ሴኔጋል ከምድቡ ያልፋሉ!!!

 

ግሩፕ  C አይቮሪኮስት፣ሞሮኮ፣ዲ. ኮንጎ፣ቶጎ

አይቮሪኮስት:-

ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ( defending champions) ሃገር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ወርቃማ ትውልዷን ተሰናብታ በወጣቶች የተገነባውን ቡድኗን በመያዝ ክብሯን ለማስጠበቅ ወደ ጋቦን ምታቀና ይሆናል። የቱሬ ወንድማማቾችን ጨምሮ እነ ዲዲዬ ድሮግባን በመያዝ የሚታወቀው ቡድን አሁን ሰርጂ ኦሪዬ፣ ኤሪክ ቤሊና ዊልፍሬድ ዛሃን የመሳሰሉ ወጣት ተስፈኞችን በቡድኑ በማካተት ውድድራቸውን ከቶጎ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ይከፍታሉ። በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ተዘዋውረው ያሰለጡትና አሁን ‘ዝሆኖቹን’ ይዘው በአፍሪካ ዋንጫው ከሚቀርቡት የ57 አመቱ ፈረንሳዊ ሚሼል ዱስዬር አይቮሪያውያኑ ብዙ ይጠብቃሉ።

ሞሮኮ:-

የአትላስ አናብስቱ የውድድሩን ዋንጫ ከሁለት የተያዩ ሃገራት (ዛምቢያ 2012፤ ኮትዲቯር 2015) ጋር ወደ ላይ ከፍ ማድረግ የቻለውንና አስማተኛው( the magician) በሚል የተሞካሸውን ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ ማምጣታቸው ለቡድኑ ጥራትን እንደሚያክልበት ተንታኞች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አሰልጣኙ አሁን እያጋጠመው ያለው የተጫዋቾች ጉዳት በብ/ቡድኑ ላይ አሉታዊ ጥላን እንዳያጠላ እሰጋለሁ ሲል ኢያን ሃውኪ ይገልፃል። የጫወታ አቀጣጣዩን የኒስ አማካይ ዩኒስ ቤላንዳን ( photo) ጨምሮ እንደ ሱፊያን ቡፋል ( ሳውዝአምፕተን) እና አምራባት ( ዋትፎርድ) የመሳሰሉ ቁልፍ ተጫዋቾች ለውድድሩ ብቁ አለመሆን ለሬናርድ ጭንቀት ቢሆንም የአህጉሪቱን የእግር ኳስ ባህል በሚገባ ያውቀዋል የሚባልለት አሰልጣኝ እንደመሆኑ የምድቡን ፉክክር ወደላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ይጠበቃል።

ዲ. ኮንጎ:-

ቁልፍ ተጫዋቻቸውን ያኒክ ቦላሲን በጉዳት ቢያጡትም ኮንጋውያኑ ጠንካራ የቡድን ስብስብ፣ ጠንካራና ጨዋታዎችን ማሸነፍ የሚችል አሰልጣኝ ባለቤት በመሆናቸው ትኩረትን እንደሚስቡ ተጠብቋል። ፍሎረንት ኢቤንጌ ከሃገሩ ኮንጎ አልፎ በሩቅ ምስራቅ የእግር ኳስ አብዮትን በማቀጣጠል ላይ በምትገኘው ቻይና ጭምር የማሰልጠን ልምድን ማካበቱ ሃላፊነትን መውሰድ የማይፈራ እንዲባል ያስቻለ ሲሆን የዚህ አሰልጣኝ ብቃት ከግምት ሲገባም የመካከለኛው አፍሪካዋ ሃገር የውድድሩ ክስተት ልትሆን የምትችልበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን መገመት ይቻላል።

ቶጎ:-

አሁንም አንጋፋውን አጥቂዋን ኢማኑዌል አዲባየርን የያዘችው ቶጎ ከምድቡ ሃገራት አናሳ ትኩረት ያገኘች ሆናለች።

ግምት:- አይቮሪኮስት እና ዲሪ. ኮንጎ ከምድቡ ያልፋሉ።

 

ግሩፕ  D- ግብፅ፣ጋና፣ማሊ፣ዩጋንዳ

ግብፅ:-

እ.ኤ.አ 2010 አፍሪካ ዋንጫውን ለ3ኛ ተከታታይ ጊዜ ካሸነፉ በኃላ ባለፉት 3 ተከታታይ ውድድሮች አለመታየታቸው ግብፃውያኑን እንግዳ ያስመስላቸዋል ሲል የሚገልፀው ጋዜጠኛ ኢያን ሃውኪ በሃገሪቱ የተከሰተው የፓለቲካ አለመረጋጋት ለዚህ ውድቀት ዐበይት ምክንያት እንደነበርም ያስታውሳል። እጅግ በጣም ፈጣኑን አጥቂ ሞሃመድ ሳላህን የያዙት ፈርኦኖቹ የተጋጣሚዎቻቸውን የተከላካይ በር እንደሚፈትኑ ከወዲሁ ቅድመ ግምት አግኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦችን በማሰልጠን ውጤታማ የነበሩት አዛውንቱ አርጀንቲናዊ ሄክቶር ኩፐር ግብፅን ከተረከቡ ወዲህ ብ/ቡድኑ የውጤት መስመሩን እንዳገኘ በመታመኑ ኩፐር በጋቦን ጠንካራዋን ግብፅ የመመለስ ሃላፊነትን ተሸክመዋል።

ጋና:-

ድራማዊ በነበረ መልኩ የ2015 አፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜን በፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈው ያጡት ጋናዎች ከዚህ ውድድር ብዙ ይጠብቃሉ። 100ኛ ጨዋታውን ለሃገሩ ለመፈፀም የተቃረበውን አሳሞሃ ጂያንን ጨምሮ አንድሪው አየውን የመሳሰሉ ነባር ተጫዋቾች በቡድኑ መገኘታቸው ለእስራኤላዊው አሰልጣኝ አቭራም ግራንት የዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ ሊረዳቸው እንደሚችል ይታመናል።

ማሊ:-

በ 2012 እና 13 በተካሄዱት ተከታታይ አፍሪካ ዋንጫዎች ወቅት ግማሽ ፍፃሜ ከደረሰው ቡድን በመጠኑ የተቀየረ የሚመስለው የማሊ ቡድን በምድቡ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ የማይችልበት ምክንያት እንደማይኖር ተጠቅሷል።

ዩጋንዳ:-

‘ዘ ክሬንስ’ ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ መድረክ ከታዩ 39 አመታት ቢያልፉም የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆኑበትንና በአስተናጋጅነት የተካፈሉበትን የያኔውን ውድድር እያሰቡ በጋቦን መልካም የውድድር ጊዜን የሚያሳልፉበትን ተስፋ ይሰንቃሉ። ገና ከወዲሁ በካፍ አማካይነት የሚሰጠውን የአመቱ ምርጥ ብሄራዊ ቡድን ሽልማትን በአቡጃ ያገኙት ዩጋንዳዎች በበርካቶች የውድድሩ ክስተት ይሆናሉ በሚል ግምትን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

 

በ በረከት ፀጋዪ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.