“ዋጋ አልባ ክፍያ”

0
1030

እኔና ጓደኛዬ የአምስት ዓመት የሞት ሽረት ትግል ፍፃሜ ማብሰሪያ በሆነው የምረቃ መፅሔቱ ላይ የተሰደሩ ፎቶዎችን ከአስገራሚና አስቂኝ የተመራቂዎች አባባል ጋር እያዋዛን ስንመለከት የተወሰኑ ገፆች አገላብጠናል፡፡ ከገረሙኝ መካከል “ድንጋይ ፈላጭ ኢንጂነር ስላረከኝ ባላመሰግንህስ? ” (ከኮብልስቶን ማለቱ ይሆናል)፣ ከተዘቀዘቀ  ፎቶ ስር “ እንደ ዘቀዘቃችሁኝ ይኸው ዘቀዘቅኳችሁ” እውነቱን ነው ባይዘቀዘቁ ፎቶውን መለየት ይከብድ ነበር “የመማሬ መጨረሻ  ቀሚስ በመልበስ ተጠናቀቀ” ዘይገርም፡፡

ካሳቁኝ መካከል “ዞሮ ዞሮ መግቢያው ጭረሮ” “ሁለት ኮርስ ይቀረኛል ገና ነኝ፣” የምርቃና ሰበብ ተዛዘመ “እማ ጉድሽ ላይፍ ሰይፍ ሊሆንብኝ ነው”፣ “መመረቅ ብርቅ ነው እንዴ እና የመሳሰሉ”፡፡

አሁን የመፅሔቱን እኩሌታ አልፈናል፤ የጓደኛዬ ፎቶ ብቅ አለ ትኩር ብሎ ቢመለከተኝም እኔ ግን ምን እንዳሰፈረ ለማንበብ ከፎቶው ስር አፈጠጥኩ “ወንድሜ ብዙ ሰጠኸኝ ግን አልተቀበልኩህም” ይላል፡፡ ትንሽ እንደማሰላሰል አልኩና ምን ለማለት እንደፈለገ እንዲያብራራልኝ በሚጠይቅ እይታ ተመለከትኩት፡፡ በርግጥ ጓደኛዬ ሀሳባዊ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡

ከጥቂት የአርምሞ ቅጥፍ ቆይታው በነቢብ ተመለሰ፡፡ “ጓደኛዬ”፡- አለኝ ወደ አይኖቼ ብሌን ማህፀን አይኖቹን አስርጎ፡፡ “ዋጋ ምንድን ነው? ከመስጠትና ጎን ሁሌም ዋጋ የምትቆም ይመስልሀል? በወንድሜ መክፈል የታየው መስጠት እንጅ ዋጋ እንዴት ይሆናል? ‘ለዚህ ያበቃሁህ እኔ ኮ ነኝ’ የተሰኘች የዘመናት የሱ እኔን የማስበርገግያ የጉራ ሽመል የተገዛበት ከንቱ ልግስና እንጂ፤ ለኔ ተብሎ የተበረከተ በልቤም ውስጥ ዋጋ የተሰኘ የክብር ስም የሚያጎናፅፍ፤ የፍቅር ምፅዋት አይምሰልህ፡፡ ወንድሜን ከኔ በላይ ራሱም ራሱን አያውቅም፡፡

ባይሆን ዋጋን በህያው ቅዠቴ ውስጥ ስጮህ ሦስተኛው ጆሮዬ የሰማውን ልንገርህ፡፡

ዋጋ፡- የየትኛውም ልግስና ዋጋነት የሚመዘነው በወቅቱ ክሳት እንጂ በክፍያ ውፍረት አይደለም፡፡

የቱንም ነገር ስትሰጥ የዋጋነትን ክብር ለችሮታህ አንተ  አትስጠው፡፡ ይልቅ ስለዚህ ነገር አብዝቶ የሚያውቀው ተቀባዩ ነውና፡፡ ዝናብ ለበልግ ደምወዙ ቢሆንም ለፀደይ ግን በእንቅልፍ ዘመን የበቀለች የሌሊት ጀንበር ከመሆን ማንም አያስጥለውም፡፡

 

ዛሬ ደጇ ላይ ብቅል ላሰጣች ባልቴት የነገው ፀሐይ ምኗ ነው?

ጥላም በጨረቃ የእንቅፋት ወገን መሆንን ትቶ ለእግርህ ብርቱ ጫማ እንዴት ይሆንለታል?

በበረሀም ለከረመች ነፍስ ለአፏ ከውሃ የጣፈጠ ማር ከየት ይገኝላታል፡፡ ቢገኝም እሱ ላለ ውሃ እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡

ለበዓል አሮጌ ልብሱን አስጥለህ በአዲስ ልብስ ከአስጌጥከው ይልቅ በቁር ዘመን እላቂ ጨርቅ ያዋስከው ሰው ውለታህን በምን ይከፍለው ይሆን?

ልቡ በተሰበረበት ሌሊት የበሩን ደጃፍ በሁለት እጆችህ ተደግፈህ የጥርሶችህን መስኮት ከፍተህ ያላገጥክበት ምስኪን ሰው፤ ለዚህ ክፉ ስጦታህ ዋጋውን ካልመለስክ  እሱ ቅዱስ መሆኑን አትጠራጠር፡፡

የደምም ዋጋነት ከገነት የተባረረ አዳም እስከሌለ ድረስ ቀይ ውሃ ከመሆን ማን ሊያድነው አይችልም፡፡

ወንድሜ ሰጠኝ እኔም ወሰድኩ  እንጅ አልተቀበልኩትም፡፡ ባልማር ለወንድሜ ወደ መቃብር የሄድኩ የግብዓተ መሬቱ ቀን ያለፈበት የከረፋ ሬሳ አይነት እንደሆንኩ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን መማር ለኔ ምኔ እንደሆነ ከኔ በቀር ለኔ ማን ሊነግረኝ ይችላል? መማር ለኔ መማር ብቻ እንጂ የመኖሬ ትርጉም አይደለም ለወንድሜ እንደሆነው ሁሉ፡፡ ስጦታዎቹ ሁሉ ከኪሱ እንጂ ከነፍሱ ያልወጡ ዋጋ አልባ ክፍያዎች ነበሩ፡፡

ንግግሩን እንደፈፀመ ያወኩት የመፅሔቱን ቀጣይ ገፅ ሊገልጥ ሲል ነው፡፡ እኔም አፌ ውስጥ የቆየውን ምራቄን ገርገጭ አድርጌ ካወራረድኩ በኋላ ይበቃል ያየነው አሁን ስለ ዋጋ የነገርከኝን እፅፈዋለሁ እደገና ንገረኝ አልኩት እሱም፡

“የተናገርኩት ነገር ዋጋነቱ ቅድም ሲናገር ነው፡፡ አሁን እንኳ ጊዜው ስላለፈበት ወሬ ከመሆን የዘለለ ዋጋ አይኖረውም” አለኝ፡፡ እኔም ደግሞ እንደማይነገረኝ ስላወኩ የተናገራቸው ነገሮች ሳይጠፉኝ በሶስተኛው ጆሮዬ እደገና ላስተውላቸው ወደ መኝታ ክፍሉ ጥየው አመራሁ፡፡

ለኔ እሱ ከህይወት ኮሌጅ ከተመረቀ በርግጥ ቆይቷል፡፡ በውኑ መማር ዋጋ የሚኖረው በመረጃ ጎተራነት ከፍ ስንል ሳይሆን በማወቅ ጥላ ስር በፍቅር ስንጠለል ብቻ ነው፡፡

አክሊሉ ማጋ

ታህሳስ 2009 ዓ.ም

 

 

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.