በመርካቶ በ200 ሚሊዮን ብር የከተማ አውቶቡስ መናኸሪያ ሊገነባ ነው

0
929

በመርካቶ ገበያ በ200 ሚሊዮን ብር የከተማ አውቶቡስ መናኸሪያ ለመገንባት ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው፥ ለግንባታው ሲ.ጂ.ሲ.ሲ.ኦ.ሲ ከተባለ የቻይና የግንባታ ተቋራጭ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የጽህፈት ቤቱ የትራንስፖርት ስራ ክፍል ኃላፊ አቶ ይሄይስ ገብረስላሴ እንዳሉት በ4 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የሚገነባው መናኸሪያ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ተገንብቶ አገልግሎት ይጀምራል፡፡ግንባታው የነዋሪዎችን የትራንስፖርት እጥረትና የዜጎችን እንግልት ከመቅረፉም ባሻገር የተበታተነ አገልግሎትን ያስቀራል ተብሎ ይጠበቃል።

መናኸሪያው ተሳፋሪዎች የሚፈለጉትን የገበያ አገልግሎት የሚያገኙበት ሱቆችና የገበያ ማዕከላትን የያዘ ሲሆን ለተሳፋሪዎች ምቹ እንደሚሆን ይጠበቃል።መናኸሪያው ለተሳፋሪዎች የአውቶብሶቹን ቁጥር፣ መነሻና መድረሻ ሰአት እና የቦታ መረጃ የሚያሰጥና ዘመናዊ መጠለያም የሚኖረው ነው።

ግንባታውን የሚያከናውነው ድርጅት የስራውን አዋጭነት የዲዛይን ግንባታ ማስተካከያ ስራ ከጽህፈት ቤቱ ጋር ያከናወነ ሲሆን ስራውን ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁ ታውቋል።

ጽህፈት ቤቱ የህዝብ ትራንስፖርቶች በቀላሉ ለተጠቃሚው አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።በቀጣይም ጽህፈት ቤቱ ተመሳሳይ ችግር የሚታይባቸውን አካባቢዎች በመለየት አዳዲስ ግንባታዎች ያካሂዳል ብለዋል።

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.