የ11ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኞች ውል መፈፀሚያ እስከ ታህሳስ 5 ቀን 2009 ዓ.ም እንዲራዘም ተደርጓል::

0
1163

የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኞች ውል እንዲፈጽሙ የተጀመረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት መራዘሙን የአዲስ አበባ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የቤት ዕድለኞች ውል እንዲፈጽሙ እስከ ህዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ቀነ ገደብ የተቀመጠላቸው ቢሆንም እስከ ታህሳስ 5 ቀን 2009 ዓ.ም እንዲራዘም ተደርጓል።

በተራዘመው የጊዜ ገደብ ግዴታቸውን የማይወጡ ዕድለኞች ቤቱን እንደማይፈልጉት ተቆጥሮ ለሌሎች ዕድለኞች በዕጣ የሚተላለፍ መሆኑን ኤጀንሲው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ሽመልስ ታምራት እንደገለጹት ዕድለኞች የሚዋዋሉበት ቀን የተራዘመው በታቀደው መሰረት አገልግሎቱን ለማዳረስ ባለመቻሉ ነው።

አገልግሎቱ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኞችን የቤት ውል፣ የይዞታ አስተዳደርና የባንክ ብድር በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር እንደሆነ ነው ስራ አስኪያጁ የተናገሩት።

በአገልግሎቱ እስካሁን 23 ሺህ 465 ሰዎች የሚፈለግባቸውን አሟልተው የቤት ባለቤትነታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን 7 ሺህ 169 የሚሆኑት ደግሞ ውለታ አለመፈጸማቸውን አብራርተዋል።

የመዋዋያ ቅጹን ከወሰዱ 29 ሺህ 500 የቤት ዕድለኞች መካከል 6 ሺህ 35 የሚሆኑት ቅጹን ያልመለሱ ሲሆን 1 ሺህ 134 የሚሆኑት ደግሞ ቅጹን አለመውሰዳቸውንም ነው የጠቆሙት።

ለአገልግሎቱ መራዘም የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የዕድለኞች የስም ስህተት፣ ቅፅ ወስዶ ውሉን አለመፈጸምና ቅጹን አለመውሰድ ሥራ አሥኪያጁ በምክንያትነት አንስተዋል።

በተጨማሪም ዕድለኞች የ “ይራዘምልን” ጥያቄ ለኤጀንሲው ማቅረባቸውን ተከትሎ እንዲራዘም መደረጉን ነው የገለጹት።

በተራዘመው የጊዜ ገደብ ግዴታቸውን የማይወጡ ዕድለኞች ቤቱን እንደማይፈልጉት ተቆጥሮ ለሌሎች እድለኞች በዕጣ የሚተላለፍ ይሆናል።

ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውጪ የሚስተናገዱት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘና ወታደራዊ ግዳጅ ላይ የሚገኙ ዕድለኞች እንደሆኑም ሥራ አሥኪያጁ ግልጽ አድርገዋል።

በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው ዕድለኞች ሆነው በስማቸው ላይ የፊደል ግደፈት ያጋጠማቸውን ግለሰቦች ስም እያስተካከለ ይገኛል።

የአንድ መስኮት አገልግሎት ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም በተካሄደው የ11ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ዕድለኛ የሆኑ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች በአዲስ መልክ መጀመሩን ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.