የተጣመመ ዛፍ – የተጣመመ ትውልድ

0
801

ድብርታሙ ቀን ጓዙን አራግፎ ወደመጣበት ሲጓዝ… ፀሃይም በቃጠሎ ስትጠብስ የነበረውን የአዲስ አበባ ህዝብ ተሰናብታ ወደቤቷ ስታዘቀዝቅ እና ምሽቱ በቦታዋ ሲተካ ከቤቴ ወጥቼ ጉዞ እጀምራለሁ፡፡ በቀን መውጣት ደስ አይለኝም፡፡ ከሰማይ ፀሃይቱ፣ ከመሬት አስፋልቱ፣ ከመሃክል ደግሞ የሰዉ ባህሪይ ያቃጥላል፡፡ መሸትሸት ሲል ግን ከተማዋ ትተነፍሳለች፡፡ ሰዉም ይቀዘቅዛል፡፡ እርሱን ተስፋ አድርጌ ልውጣ እንጂ ዘመነኛዋ ቦሌ ግን አትተነፍስም፡፡ ሁሌ ሳስተውለው ለአገሩ ሲመሽ ለርሷ ግን የበለጠ የነጋላት ይመስላል፡፡ ምሽቱ ብዙም ባይገፋም ሰዉ ግን… መኪና ያለው በመኪና… በእግሩ የሚሄድ በእግሩ… ወደ መሸታ ቤት ይገሰግሳል፡፡ በቀን አንድም የማይስማማበት የሌለው ሰው ሁሉ በማታ ግን አንድ ግብ ያገኛል፡፡ መሸታ ቤቶቹም ቢሆኑ ላለማሳፈር በሚመስል አኳኋን ኑሮን ከነጓዟ ለአንድ ምሽትም ቢሆን የመርሳትን ተስፋ ለመሸጥ አቅል የሚሰውረውን አልኮል በየመልኩ ደርድረው እና ታምቡር በሚበጥስ ሙዚቃ ታጅበው ደንበኞቻቸውን ይጣራሉ፡፡

ዘውትር ስወጣ አስፋልቱን እየታከኩኝ መንገዴን አቀናለሁ፡፡ ከተማይቱ ከተፈጥሮ ህግ በተገላቢጦሽ መስራቷ ግልጽ ከሆነልኝ ቆይቷል፡፡ ፀሃይ ብርሃንን እና ተስፋን እንደምትሰንቅ በተቃራኒው ደግሞ ጨለማው መደናበርን እና ተስፋ መቁረጥን እንደሚሰብክ ውስጣችን ሹክ ቢለንም… የሸገር ኑሮ የተፈጥሮን ህግ ቀልብሷል፡፡ ምሽቱ ሲሰፍን የሰዉ ድብቅ ባህሪይ ይጋለጣል፡፡ ስርዓት አልበኝነቱ፣ ልቅነቱ፣ ሴሰኝነቱ፣ ወንጀሉ ሁሉ ከየግለሰቡ ገመና ውስጥ የሾለ ጥርሳቸውን አግጥጠው ይወጣሉ፡፡ ጠዋት ሱፉን ለብሱ በታክሲ ውስጥ ሂሳብ የከፈለላችሁን ታታሪ ሰራተኛ ሌሊት ላይ ዙሪያ ገባውን በአይኑ እያማተረ እና በወሲብ ስሜት እየተክለፈለፈ ወደ መሸታ ቤት ሲገባ ታዩታላችሁ፡፡ ጎህ ሲቀድ ከበር ላይ ባለቤቷን ተሰናብታ ወደስራዋ ስታቀና የምታውቋት እመቤት በምሽቱ ባሏ ካልሆነ ሰው ጋር በማበር የጋብቻ ሰነዷ ላይ ስትጨፍር ታስተውላላችሁ፡፡ ዶሮ ሲጮህ ተነስቶ እና በዩኒፎርሙ አጊጦ የአገሪቷን ተስፋ ሊያቃና ወደ ትምህርት-ቤት ሲገሰግስ ያያችሁት ወጣት በምሽት ሰክሮ የሰዉን እናት በስድብ ሲዘረጥጥ ትታዘባላችሁ፡፡

አዲስ አበባን “ዘመነኛ” ቦሌን ደግሞ ለይቶ “አሪፍ ሰፈር” ያደረገው ይኼው ነው፡፡ ዘመናይ የሚለው ቃልም ከትውልዱ ጋር አብሮ በማበር የቀድሞ ማንነቱን አራግፎ በሴሰኝነት መጠመቁን ማሳያ ግልጽ መስታወት ይመስለኛል፡፡ ወደድንም ጠላንም “የድሮ” ማለት “መሻር ያለበት” ከሚለው ቃል ጋር ትይዩ ትርጉምን በሚሰጥ ትውልድ ውስጥ አድገናል፡፡ ማሳዘን የሚገባው ማሳዘን አቁሟል፡፡ ማሳፈር የሚገባው የሚያስሞግስ ሆኗል፡፡ ትውልዱ ብቻ ሳይሆን ቃላቶቻችንም ህብረ-ቀለማቸውን ከድተውታል፡፡ የአዲስ አበባ ጭንቅንቅ ሲቀንስ… ትንፍስ ሲል… ሲመሻሽ… ወደውጪ መውጣትን የምመርጠው ታዲያ ለዚሁ ነው፡፡ መራራው እውነት አይኑን አፍጥጦ የሚጋፈጠን በምሽት ነው፡፡ ምንም ቢሆን ከጣፋጭ ውሸት መራራ እውነት ይሻላልና፡፡

የማታውን ገጽታ እያስተዋልኩ ስራመድ ዘውትር የምጠይቀው ጥያቄ አለኝ፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነ እላለሁ፡፡ ፍሬው ሲተከል ንጹህ ሆኖ ተተክሎ ነበር፡፡ አፈር፣ ውሃ፣ ፀሃይ አግኝቶ እና ተኮትኩታ አድጓል፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ ታዲያ ስለምን ዛፉ ተጣመመ? ጥፋቱስ የማነው? ሃላፊነቱንስ የሚወስደው ማነው? መጣመሙስ ከየት ጋር ተጀመረ? አንድ ትውልድ ሲያልፍ ሌላ ትውልድ ይተካል፡፡ የህይወት መርህ ነውና ሳይተካኩ ማለፍ አይታሰብም፡፡ ቀደምት ትውልዶች የአባትና የእናቶቻቸው ግልባጭ ቢሆኑም የራሳቸውን ማንነት ግን በራሳቸው መምረጥ ችለው ነበር፡፡ የኛ ትውልድ ጋር ስንደርስ ታዲያ ለምን እሴቶቻችን ወራጅ አለ ማለት ጀመሩ? በእርግጥ ይህ ትውልድ የራሱ አይደለም፡፡ ራሱን አልተከለም፣ ራሱን አልተንከባከበም፣ ራሱንም አልኮተኮተም፡፡ በዘረመሉም ሆነ በአስተሳሰቡ ያለፈው ትውልድ ግልባጭ ነው፡፡ ሆኖም ግን ያለፈው ትውልድ ህላዌነት የለውም፡፡ መፍቀሬ-ነፍስ ሳይሆን መፍቀሬ-ሥጋ ነው፡፡ ቀን ሲገፋ እና ወቅቶችም ሲለዋወጡ ዛፉ መጣመሙን ቀጥሏል፡፡

ንጹህ ፍሬ እንዴት ጠማማ ዛፍ ሊወልድ ይችላል? መንፈሳዊ ህብረተሰብ እንዴት ሥጋዊ ትውልድ ሊያፈራ ይችላል? ግብረገባዊ ትውልድ እንዴት ኢ-ግብረገባዊ ትውልድ ሊያስከትል ይችላል?

ይህ ሁሉ ለምን ሆነ?

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.